18ኛው የፈለገ-ኪን የኪነ-ጥበብ መድረክ ባለቅኔው ገሞራውን በመዘከር በድምቀት ተከናወነ


የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም | አዲስ አበባ

በየወሩ የመጨረሻ ቅዳሜ በኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር (ኢ/ዓ/ብ/ማ) አዘጋጅነት የሚቀርበው “ፈለገ-ኪን” የኪነ-ጥበብ መድረክ፤ 18ኛ ጉዞውን ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 28 ቀን በስኬት አከናውኗል። “ታላላቆችን ማክበርና ታናናሾችን ማጀገን” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው በዚህ መድረክ፣ በኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄና በስነ-ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ በቅጽል ስሙ “ገሞራው” በመባል የሚታወቀው ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሐንስ ተዘካሪ ሆኖ ውሏል።

የክብር እንግዶችና የታሪክ ድርሳናት

የዕለቱ የክብር እንግዳ አንጋፋው የግጥምና ዜማ ደራሲ አለማየሁ ደመቀ ሲሆኑ፣ የባለቅኔው ገሞራው የቅርብ ወዳጆችና ቤተሰቦችም በመገኘት መድረኩን ባርከዋል። የክብር እንግዳው ደራሲ አለማየሁ ደመቀ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የፈለገ-ኪን መድረክ አንጋፋ ደራሲያንን በመዘከርና ልምዳቸውን ለጀማሪዎች እንዲያካፍሉ በማመቻቸቱ የሚደነቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ወጣት ባለተሰጥኦዎች ለታላላቅ ዓላማዎች ራሳቸውን እንዲያበቁና ጠንክረው እንዲሰሩ መክረዋል።

የጥበብ ድግሱ ይዘት

በማኅበሩ ግቢ (ሞቢሊቲ) በተካሄደው በዚህ መርሃ-ግብር ላይ፦

  • ባለተሰጥኦ ዓይነስውራንና አይናማ ወዳጆቻቸው የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን አቅርበዋል።
  • የማኅበሩ ኩራት የሆነው “ወጋገን ባንድ” ጥዑም ዜማዎቹን በማሰማት ታዳሚውን አዝናንቷል።
  • ደራሲ አለማየሁ ደመቀ ለቀረቡላቸው የሕይወት ተሞክሮና የሥራ ልምድ ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

ምስጋናና የቀጠሮ ጥሪ

የፈለገ-ኪን አዘጋጅ ኮሚቴ ለመላው ታዳሚዎች፣ ለጥበብ ባለሙያዎችና ለደጋፊዎች ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል። ቀጣዩ መርሃ-ግብር መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም በወሩ የመጨረሻ ቅዳሜ የሚከናወን መሆኑን እየገለጽን፣ ሁላችሁም የጥበብ አፍቃሪያን ተጋብዛችኋል።


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Skip to content