የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር ሰኔ 14 ቀን፣ 2017 አመተ ምህረት፣ በአዳማ ከተማ ፣ “አካታች የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና” በሚል ርዕስ የአንድ ቀን ሥልጠና አካሄደ። ስልጠናው አይነ ስውራን በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መስጫ ተቋማት ገብተው ለመማር የሚገጥሟቸው መሰናክሎችን ለመለየት፤ በባለድርሻ አካላትና በኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር መካከል ቅንጅታዊ አሰራርን ለመፍጠር፤ በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት መካከል የእርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና (TVET) ስርአተ ትምህርትን ለዓይነ ስውራን ተደራሽ ለማድረግ መወሰድ ስለሚገባቸው ተግባራዊ እርምጃዎች መመካከርን ያለመ ሲሆን፣ በስልጠናው ከTVET ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ባለድርሻ አካላት ማለትም፥ በአዲስ አበባ፣ ሰበታ እና አዳማ ከሚገኙ 17 ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች የተውጣጡ ተወካዮች፣ ከፌዴራል የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ እና ክህሎት ቢሮ፣ ከኦሮሚያ ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ ከኦሮሚያ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ፣ እና ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋም (FTVETI) የተወጣጡ ቁልፍ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
ስልጠናው የማህበራችን የህዝብ ግንኙነት የአባላት እና ቅርንጫፎች ጉዳይ ሀላፊ በሆኑት በአቶ ገብሬ ተሾመ የእንኳን ደህና መጣችሁና የመክፈቻ ንግግር የተጀመረ ሲሆን፣ አቶ ገብሬ ባደረጉት ንግግር አይነ ስውራን በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የቀለም ትምህርት ለመማር እንኳን ክልከላ ተደርጎባቸው ከብዙ ትግል በኋላ እንዲማሩ የተፈቀደላቸው መሆኑን፤ ለዚህ ደግሞ ከእያንዳንዱ አይነ ስውር ጀምሮ በማህበር በተደረገ ርብርብ ስኬት ማስመዝገብ መቻሉን፤ የሙያና ቴክኒክ ትምህርትና ስልጠናንም በተመለከተ በንጉሱ ዘመን እና ከዚያ በኋላ ባሉ ጥቂት አመታት እንደ መጥረጊያና ምንጣፍ፣ ዣንጥላ፣ ፊዚዮቴራፒና በመሳሰሉ ዘርፎች አይነ ስውራን ይታወቁ እንደነበር በመጥቀስ ታሪካዊ ዳራውን አውስተዋል። የሙያና ቴክኒክ ጠቀሜታ እንብዛም ባልታወቀበት ዘመን አይነስውራንን በዘርፉ ለማስጠቀም ጥረት የመደረጉን ያህል በተቃራኒው ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በተሰጠበት በዚህ ዘመን ደግሞ አይነ ስውራንን በዘርፉ ስለማካተት በቂ ትኩረት አለመሰጠቱ የመንግስትና በዘርፉ የሚሰሩ ባለ ድርሻ አካላት ክፍተት መሆኑን በማንሳት፣ የዛሬው ስልጠና ይህንን ክፍተት የማሳየትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የማመላከት አላማ ያለው መሆኑን በመግለጽና ተሳታፊዎች ለስልጠናው ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉ በማሳሰብ የመድረኩን መከፈት አብስረዋል።
በመቀጠልም ወደ ዋናው ስልጠና የተገባ ሲሆን ስልጠናው የተሰጠው የህግ ባለሙያ እና የአካል ጉዳተኞች መብት አማካሪ በሆኑት በእጩ ዶክተር ይልቃል ሀሳቤ አማካኝነት ሲሆን እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2021 በወጣው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲና እስትራቴጂ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል። ከዚህም ባሻገር በቡድን ውይይትና በተሞክሮ ልውውጥ የተሳታፊዎች ግንዛቤ እንዲያድግ ጥረት ተደርጓል። ከተለያዩ ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች የመጡ ተሳታፊዎች እንደገለጹት ከሆነ፣ በእየተቋማቱ ለአካል ጉዳተኞች አንዳንድ የሥልጠና ዕድሎች ቢኖሩም፣ ዓይነ ስውራንን ማካተት ግን አሁንም በጣም ውስን እንደሆነ እና በአብዛኛው በአጭር ጊዜ ሥልጠናዎች ብቻ የተወሰነ መሆኑን አብራርተዋል። ለምሳሌ ምስራቅ ፖሊቴክኒክ ለዓይነ ስውራን ተማሪዎች የኮምፒውተር ስልጠና ሰጥቷል፤ እንጦጦ ፖሊቴክኒክ በአሁኑ ጊዜ በመደበኛ የሙዚቃ ፕሮግራማቸው አንድ ዓይነ ስውር ተማሪ እንዳለ ገልጾ ሰባት ዓይነ ስውራንን በተለያዩ አጫጭር የስልጠና ፕሮግራም ማሰልጠናቸውን ተናግረዋል። ንፋስ ስልክ ፖሊቴክኒክ ዓይነ ስውራን ተማሪዎችን በኮምፒውተር ዘርፍ ለማስተማር ሰልጥነው ዝግጁ የሆኑ መምህራን ቢኖሯቸውም ከዓይነ ስውራን የቀረበላቸው የእንሰልጥን ጥያቄ የለም ብለዋል። ሰበታ ፖሊቴክኒክ በአንፃራዊነት የተሻለ ቁጥር ያላቸው ከፊል እይታ ያላቸው አይነ ስውራንን በሞባይል ጥገና ዘርፍ በማስተማር ያለውን ተሞክሮ ለሌሎች ኮሌጆች አካፍሏል።
ሁሉም ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች በተመሳሳይነት ያነሱት ሀሳብ መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በተቻለ መጠን አካል ጉዳተኞችን ለማካተት እየሞከረ ቢሆንም፣ የተመዝጋቢ አካል ጉዳተኞች ቁጥር ግን በጣም አነስተኛ መሆኑን ነው። በተለይም አይነ ስውራን ወደ እነዚህ ተቋማት ስለማይመጡ ቁጥራቸው ከሌሎች አካል ጉዳተኞችም በእጅጉ ያነሰ መሆኑን ተናግረዋል። ስለዚህ አይነ ስውራን ስለ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ ሊሆን እንደሚችል የሚጠረጥሩ መሆኑን ሳይሸሽጉ ገልጸዋል. ከውይይቱ በመቀጠል የማህበራችን የኢኮኖሚ ማጎልበት አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ አያሌው ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገራት የተወሰዱ ተሞክሮዎችን በማንሳት አይነ ስውራን ሊሰማሩባቸው የሚችሉ ዘርፎችን ያመላከቱ ሲሆን በቀጣይ የስራ ክፍላቸው በስልጠናው ከተገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት የተጠናከረ ጥናት በማካሄድ ዘርፎቹን ማስፋት የሚያስፈልግ ስለመሆኑ አጽእኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ሥልጠናው የተለያዩ ውጤቶች የተመዘገቡበት ሲሆን፤ በመጀመሪያ ደረጃ ተሳታፊዎች ዓይነ ስውራን ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸው እንደ ተደራሽ ያልሆኑ የትምህርት ቁሳቁሶች፣ የድጋፍ ቴክኖሎጂዎችና ለአስተማሪዎች በቂ የሆነ ሥልጠና አለመኖር የመሳሰሉ ልዩ ልዩ መሰናክሎችን የተገነዘቡበት ሆኗል። በሁለተኛ ደረጃ የቴክኒክና ሙያ ስርአተ ትምህርቱን በመፈተሽ ለአይነ ስውራን አመቺ የሆኑ የስልጠናና የትምህርት መስኮችን ማካተት የሚያስፈልግ ስለመሆኑ ግንዛቤ ተወስዶበታል። በሦስተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበርን ጨምሮ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ላይ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት እጅና ጓንት ሆነው በቅንጅት መስራት የሚጠበቅባቸው መሆኑ ተመላክቶበታል።
በመጨረሻም በቀጣይ ወደ ተግባር መለወጥ ስላለባቸው ጉዳዮች ውይይት ተደርጓል። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር (ኢአብማ) አባላቱ ወደ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲመጡ ቅስቀሳ እንዲያደርግ፤ ለአይነ ስውራን ምቹ የሆኑ የስልጠና መስኮችን በአነስተኛ የዳሰሳ ጥናት በመለየት ለስራና ክህሎት ቢሮ እንዲያቀርብ፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ወደ ብሬል እንዲለወጥላቸው የሚፈልጉት ሰነድ ካለ የህትመት ወጪውን ከተቋማቱ ተቀብሎ ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲያስተናግድና ፖሊቴክኒክ ኮሌጆቹ አይነ ስውራንን በተመለከተ ድጋፍ ሲፈልጉ የማማከር አገልግሎቱን ለመስጠት ሀላፊነት ተቀብሏል። በፖሊቴክኒክ ተቋማት በኩል እስከ ዛሬ ድረስ አይነ ስውራን የሰለጠኑባቸውን ዘርፎች ለማህበሩ መረጃ እንዲሰጡ፤ ማህበሩ ለአይነ ስውራን ምቹ የሆኑ የስልጠና ዘርፎችን ለመለየት ለሚያደርገው እንቅስቃሴ አጋዥ የሆኑ ሰነዶችን እንዲያጋሩ፤ የተቋማቸውን አካላዊና መረጃዊ ተደራሽነት እንዲያሻሽሉ፤ አይነ ስውራን መማር ወይም መሰልጠን እንፈልጋለን በሚሏቸው ዘርፎች ሁሉ ተቀብለው እንዲያስተምሩ፤ የተለየ ምክር ከፈለጉ ማህበሩን እንዲያነጋግሩና ችግሮችን እንዲፈቱ መግባባት ላይ ተደርሷል። በሌላ በኩል የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና በእየእርከኑ በስሩ ያሉ መዋቅሮች ስርአተ ትምህርቱን በማሻሻልና ከመንግስት የሚጠበቁ አስፈላጊ እገዛዎችን የማድረግ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ተልእኮ ከተሰጣጡ በኋላ አቶ ገብሬ ባደረጉት የማጠቃለያና የመዝጊያ ንግግር ስልጠናው ተጠናቋል።


Leave a Reply