በባህር ዳር ከተማ የካድር ፕሮጀክትን ለመተግበር የሚያስችሉ አስቻይ ሆኔታዎችን ለማየት እና የባለድርሻ አካላትን ልየታ ለማድረግ ያለመ ለሁለት ቀናት ከሰኔ 23 እስከ 24 ቀን 2017 ዓም የቆየ ውይይትና ዳሰሳ ጥናት ተደርጓል። በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ እና የኢኮኖሚ ልማት የሚሰሩ የፕሮጀክት ሰራዎችን ለመተግበር ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በሁለቱ ቴማቲክ ክፍሎች የተሰራ ተግባር ነው።
ውይይቱ የተጀመረው ከማህበሩ የባህር ዳር ቅርንጫፍ አስተባባሪ እና የማህበሩ የጠቅላላ ጉባዔው አፈጉባዔ ጋር በጋራ በመሆን ፕሮጀክቱ ትኩረት ሊያደርግባቸው የሚገቡ አካባቢዎችን ለመለየት ተሞክሯል። በዚህም ረገድ ዓይነስውራን በብዛት የሚገኙበት የፋሲሎ ክከተማ እና የጣና ክ/ከተማ በዋንኝነት ተወስደው ነገር ግን ፕሮጀክቱ በከተማዋ በስድስቱም ክ/ከተሞች ቢሠራ የተሻለ እንደሆነ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
ለጥቆም በባህር ዳር ከተማ ከሚገኙ ለአካል ጉዳተኖች መብቶች መከበር ጋር ተያይዞ ቁልፍi ከሆኑ ከከተማ እና ከክፍለ ከተማ ተወካዮች ጋር በመብት መከበር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን፣ መልካም እድሎችን እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ በየተቋማቱ በመዘዋወር ውይይት ማደረግ ተችሏል።
በውይይቱም በበጀተ ዓመቱ ብዙ ዓይነስውራንን ጨምሮ ብዙ አካል ጉዳተኞችን መቅጠር የተቻለ መሆኑ እንደመልካም አጋጣሚ የተነሳ ሲሆን ይህንንም ማደረግ የተቻለው ማህበሩ እና ሌሎች ተቋማት ባደረጉት የአድቮኬሲ ሥራ መሆኑ ተነስቷል።
የአካል ጉዳተኞችን መብቶች በተሟላ ደረጃ ከማስከበር አንጻር ግን አሁንም በአንዳንድ የመንግስት አካላት የአመለካከት ችግር፣ የማቴሪያል አቅርቦት፣ የሥራ ቦታዎች ተደራሽ አለመሆን፣ ለአካል ጉዳተኞች በቂ በጀት አለመመደቡ እና የመሳሰሉት እንደ ተግዳሮት የሚጠቀሱ መሆናቸው ተገልጿል።
ያነጋገርናቸው የየተቋማቱ ኃላፊዎች ፕሮጀክቱ ትኩረት ሰጥቶ ቢሠራባቸው ያሏቸውን የገለጹ ሲሆን ከነዚሁም መካከል ለዓይነስውራን የሥራ ክህሎት ስልጠና ቢሰጥ፣ ለአካል ጉዳትኛ ማኅበራት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች፣ እና ከመንግስት ተቋማት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ቢሰሩ የሚሉ ኃሳቦች ይገኙበታል።
እንዲሁም ከባህርዳር ከተማ እና ከአማራ ክልል የአካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን አመራሮች ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን ፕሮጀክቱ አብሮ ለመሥራት ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ እና አቅምንም የሚጨምር መሆኑ ተጠቅሷል። ማህበሩም ቀደም ሲል የሰራቸውን ዘርፈብዙ ስራዎች በእኔነት (own) አድርጎ በክልሉ እና በከተማው ከሚንቀሳቀሱት የአካል ጉዳተኛ ማህበራት ጋር በጋራ መሥራት የሥራ እና የተጠቃሚዎች ድግግሞሽን በማስቀረት ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚቻል በውይይቱ ላይ ተወስቷል።
በውይይቱ ወቅት የሰብዓዊ መብቶች አስተግባሪ እና አብይ ኮሚቴ መቋቋሙ እና ከንቲባ ጽ/ቤትን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የመንግስት ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች መብቶች መከበር ቀናኢ መሆናቸው ለፕሮጀክቱ በስኬት መተግበር እንደመልካም አጋጣሚ የሚቆጠሩ እንደሆነ ተነስቷል። እንዲሁም፣ በአንዳንድ ተቋማት እና በማህበርሰቡ ስለአካል ጉዳተኞች የሚታየው የግንዛቤ እጥረት መኖሩ እና የአካል ጉዳተኛ ማህበራት አለመጠናከር እንደ ተግዳሮት የተነሳ ሲሆን በመፍትሄውም ፕሮጀክቱ ለመንግስት ተቋማት በህጎች አተገባበር ዙሪያ ስልጠና ቢሰጥ፣ የአካል ጉዳተኛ ማህበራት አቅም የሚያጠናክሩ ሥራዎች ቢሠሩንሚዲያን ጨምሮ ከቁልፍ የመንግስት ተቋማት ጋር አብሮ ቢሠራ የሚል ኃሳብ ቀርቧል።
በመጨረሻም ከኢሲዲዲ የፕሮጀክት ባለሚያዎች ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በውይይቱም ተቋሙ በክልሉ ብዙ ፕሮጀክቶችን እያስተገበር የሚገኝ እና ከማህበራችንም ጋር በብዛት በባህርዳር ከተማ መሥራቱ በውይይቱ ወቅት በትውስታ ተነስቷል። በከተማው ለምስራት ብዙ አስቻይ የሆኑ ጉዳዮች ቢኖሩም ነገር ግን የአካል ጉዳተኞች መብዛት በተለይም በግጭ ትአማካኝነት ወደከተማዋ መፍለስ ያለውን አነስተኛ ሀብት (resource) ለማዳረስ አስቸጋሪ እንዳደረገው፣ ነገር ግን በመናበብ አንድ ፕሮጀክት ላይ ተጠቃሚ የሆኑትን ከመደጋገም ይልቅ በመናበብ ለሌሎች ላልደረሳቸው ማዳረስ ቢቻል ጥሩ እንደሆነ እና ከማህበሩ ጋርም ቀደም ሲል የተጀመረው አብሮ የመስራት ሂደት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።
በጠቃላይም ከአካል ጉዳተኖች ጋር ተያይዞ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማትን፣ የአካል ጉዳተና ማህበራትን፣ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የመለየት ሥራ እና በፕሮጀክቱ ትኩረት እና አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ውይይት ከተመረጡ ተቋማት ጋር ማድረግ ተችሏል።

Leave a Reply