“የተቋማት ሚና ለዘላቂ የቱሪዝም ልማት” የፓነል ውይይት NBC ኢትዮጵያ


በትናንትናው እለት ማለትም ህዳር 26 ቀን 2017 አ.ም የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ “የተቋማት ሚና ለዘላቂ የቱሪዝም ልማት” በሚል ርእስ በNBC ኢትዮጵያ እስቲዲዮ ፓናል ዲስከሽን አካሂዷል። በፓናል ዲስከሽኑ ላይ እንዲሳተፍ ለማህበራችን ጥሪ የተደረገ ሲሆን ማህበራችንም በፓናል ዲስከሽኑ የሚሳተፍ ባለሙያ በመላክ ተሳትፏል።
በፓናሉ ላይ ሶስት ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን የመጀመሪያው ጥናታዊ ጽሁፍ የግሉ ዘርፍ ለዘላቂ የቱሪዝም ልማት ያበረከተውን አስተዋጽኦ በሚመለከት በዶክተር አያሌው ሲሳይ ተጠንቶ የቀረበ ነው። በጥናቱ እንደተመላከተው የግል ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶችና የጉዞ ወኪሎች በቱሪዝም ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል አሁንም በመጫወት ላይ ይገኛሉ። በሀገራችን የግሉ ዘርፍ በቱሪዝም ስራ መሰማራት የጀመረው በአጼ ዳግማዊ ሚኒሊክ ዘመን መሆኑን ያብራሩት ዶክተር አያሌው ሲሳይ፤ በቀዳማዊ አጼ ሀይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት ተጠናክሮ ከመቀጠሉም ባሻገር የኢትዮጵያ ቱሪዝም ተቋምም በ1957 አ.ም ተቋቁሟል። በሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት በአመት በአማካኝ 74 ሺህ ጎብኚዎች የነበሩ ሲሆን ደርግ በትረ መንግስቱን እንደተቆጣጠረ ይህ ቁጥር ወደ 27 ሺህ ወርዷል። በደርግ የስልጣን መገባደጃ ሰሞን የጎብኚዎች ቁጥር እንደገና ወደ ላይ አሻቅቦ ከ80 ሺህ በላይ ደርሶ ነበር። ይሁንና በኢትዮጵያ የጎብኚዎች ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበው በኢህአዲግ ዘመን 974 ሺህ እንደሆነ በጥናቱ ቀርቧል። ለእነዚህ ሁሉ እድገቶች ከፍተኛውን ሚና የተጫወተው የግሉ ዘርፍ ነው ሲሉ አጠቃለዋል።
ሁለተኛው ጥናት የመንግስት ተቋማት ሚና ለዘላቂ የቱሪዝም እድገት በሚል ርእስ በዶክተር የዚህአለም ሲሳይ የቀረበ ሲሆን አጥኚው እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት መንግስት ከምን ጊዜውም በላይ ለቱሪዝም ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል። በዋነኝነት በቱሪዝም ኢንደስትሪው የመንግስት ሚና ፖሊሲዎችንና መመሪያዎችን ማውጣት በመሆኑ መንግስት በቱሪዝም ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን የሚያበረታቱ የተለያዩ ህጎችን ማውጣቱን ተናግረዋል። በ2009 የተቀረጸው የቱሪዝም ፖሊሲ በርካታ ባለ ሀብቶች ወደ ዘርፉ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እድል እንደፈጠረም ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለ ሀብቶች የሚሰጡ የተለያዩ ማበረታቻዎችም ወደ ስራ ገብተዋል ካሉ በኋላ ሀሳባቸውን ሲያጠቃልሉ መንግስት በዘርፉ ዘላቂ ልማት ላይ ከምን ጊዜውም በላይ ከፍተኛ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
ሶስተኛው ጥናት በዶክተር ፍጹም አባተ የቀረበ ጥናት ሲሆን የግሉ ዘርፍና የመንግስት ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ለዘላቂ የቱሪዝም ልማት በሚል ርእስ የተዘጋጀ ነው። በአሁኑ ወቅት መንግስትና የግሉ ዘርፍ በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት አጥኚው፤ ቅንጅታዊ አሰራሩ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል። ይህ ውጤት የተመዘገበው መንግስት በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለ ሃብቶች ለአብነትም ሆቴል ለሚከፍቱ ከትንሿ ከማንኪያ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ማሽኖችና ተሽከርካሪዎችን ሲያስገቡ ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ በማድረጉ፤ የብድር አገልግሎት በማመቻቸቱና የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችን በነጻ በመስጠቱ መሆኑን አብራርተዋል። ከዚህ ባሻገር የግሉ ዘርፍም የተሻለ የእውቀት ሽግግር ባደረገ ቁጥር የቱሪዝም እድገቱ መሻሻሉንና ለስራ አጥ ወጣቶችም ከፍተኛ የስራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል። በአንጻሩ የተጋነነ የትርፍ ፍላጎት፣ አሰልቺ ቢሮክራሲ፣ የባለ ሀብቶች የቁርጠኝነት ማነስ, የውጪ ምንዛሪና የኮላተራል ችግር ለቱሪዝም ዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸው ተገልጿል።
ጥናቶቹ ከቀረቡ በኋላ ተሳታፊዎች አስተያየቶች እንዲሰጡና ጥያቄዎችን እንዲጠይቁ እድል የተሰጠ ሲሆን የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር የሚከተሉትን ጥያቄዎች አቅርቧል።
• የጸጥታ ችግር ዋነኛው የቱሪዝም ዘርፉ ተግዳሮት ሆኖ ሳለ አለመገለጹ ለምንድን ነው፧
• የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ለአካል ጉዳተኞች እንቅስቃሴ ምቹ እንዲሆኑ ምን ስራ ተሰርቷል፧
• በሆቴሎችና በቱሪስት መዳረሻዎች ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች ስለ አካል ጉዳተኞች ግንዛቤው እንዲኖራቸው ምን ያህል ጥረት ተደርጓል፧
• ዘርፉ ለወጣቶች የስራ እድል እንደፈጠረ ተገልጿል። ለመሆኑ ለአይነ ስውራን ስራ አጥ ዎጣቶችስ የተለዩ የስራ ዘርፎች አሉ ወይ፧
• የኮሪደር ልማት ስራዎች አንዱ አላማ ቱሪዝሙን ለማጠናከርም ጭምር እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህ አኳያ ለአይነ ስውራን ተብሎ በተለምዶ የሚጠቀሰው የእግረኛ መንገድ ላይ ያለ በቢጫ ቀለም የተሰራው መንገድ ምን ያህል የአይነ ስውራንን ችግር የሚፈታ መሆኑ ተገምግሟል፧ ከአይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር ጋርስ ውይይት ተደርጎበታል ወይ፧ የሚሉ ናቸው።
ከላይ ማህበራችን ለጠየቃቸው ጥያቄዎች ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን የጸጥታ ችግርን በተመለከተ የጸጥታን ጉዳይ አጉልቶ በሰነድ ላይ ማስቀመጡ በቱሪስቶች ላይ ሊያሳድር የሚችለው ችግር ስላለ በግልጽ አይቀመጥ እንጂ ለቱሪዝሙ ተግዳሮት መሆኑን እኛም እናውቃለን። የአካል ተደራሽነትን በተመለከተ እየተሰራበት ነው። መሻሻሎችም አሉ። ነገር ግን አሁንም በርካታ የሚቀሩ ነገሮች ስላሉ እየሰራን ነው። ለሰራተኞች ግንዛቤ መስጠትንም በተመለከተ በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ያለ ነው። ለአይነ ስውራን የሚሆን የስራ ዘርፍን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ከአንድ አካል ጉዳተኞች ማህበር ጋር በመተባበር ባደረግነው ጥናት አይነ ስውራን ቱር ጋይድ ሆነው መስራት እንደሚችሉ አረጋግጠናል። አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር እነዚህን የስራ መደቦች አስጠንቶ ቢያመጣልን ቢሮው ለማስተናገድ ዝግጁ ነው። በኮሪደር ልማት በተሰሩ የእግረኛ መንገዶች ላይ ያለውን ችግር ለሚመለከተው አካል ጥቆማ እናደርሳለን። የሚሉ ምላሾች ተሰጥተዋል።
በመጨረሻም ፓናል ዲስኬሽኑ6 ሰአት ላይ ተጠናቋል።


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Skip to content