የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጣቸው አስገዳጅ የሕግ ትርጉሞች በድምጽ ተደራሽ መደረጋቸው ቀጥሏል፡፡


በዛሬው እለት ሓምሌ 23 ቀን 2017 ዓ.ም. የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክቡር ፕሬዚደንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት ከቅጽ 19 እስከ ቅጽ 26 ያሉት እና በድምጽ ለአይነስውራን ዜጎች በማሰብ ተደራሽ የተደረጉትን የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎችን ለኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዚደንት አስረክበዋል፡፡ በርክክቡም ላይ በማህበራችን በኩል የኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር፣ የሕዝብ፣ የአባላት እና የቅርንጫፍ ጉዳዮች ኃላፊ፣ የፋይናንስ ኃላፊ እና የማኅበሩ ፕሬዚደንት ተገኝተዋል፡፡ በኢ።ፌ።ዴ።ሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኩል ክቡር ፕሬዚደንት ቴድሮስ ምህረት፣ የፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ድሪባ ፈየራ፣ የህዝብ ግንኙነት አቶ ተመስገን፣ የሬጅስትራር ዋና ሃላፊ ወ/ሮ ዙፋን፣ የፍርድ ቤቱ የኮሚኒኬሽን ባለሙያ ወ/ሮ ሰላም እና ዳኛ ሱራፍኤል ተገኝተዋል። በእለቱም ክቡር ፕሬዚደንት አቶ ቴውድሮስ ምህረት፣ ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል እስከ ቅጽ 18 ድረስ በድምጽ ተደራሽ ማድረጉን፣ ይህም ሥራ ለአይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ከመሰጠቱም በተጨማሪ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንዲሰራጭ መደረጉንና በተገባው ቃል መሠረት ቀሪ የሰበር ውሳኔዎች ማለትም እስከ ቅጽ 26 ድረስ በድምጽ ተደራሽ መደረጋቸውን ገልጸው ይህም የፍርድ ቤቱ ግዴታ በመሆኑ እና ግዴታውንም በአግባቡ በመወጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ከዚህ ሥራ ጀርባ ላሉ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዚደንት አቶ አበራ ረታ በበኩላቸው፣ ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም በማለት የደነገገው አካል ለሚመለከታቸው ሁሉ ሕጎችን ተደራሽ ማድረግ አለበት ካሉ በኋላ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ሕግ እንደመሆናቸው መጠን እነዚህን ውሳኔዎች ተደራሽ ማድረግ ስላለበት በዚህ ኃላፊነት መሠረት የሰበር ሰሚ ችሎቱን ውሳኔዎች በድምጽ በማዘጋጀት ተደራሽ ማድረጉ የሚወደስ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፍርድ ቤቱ እና ማኅበሩ በትብብር እና በቅንጅት ለመሥራት በዘረጉት ስልት መሠረት አብረው እየሠሩ መሆኑን እና ይህንን ቅንጅት ውጤታማ ለማድረግ በማኅበሩ በኩል ቁርጠኝነት መኖሩን፣ በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር በኩል የማኅበሩ ፕሬዚደንት ማኅበሩን እንዲወክሉ እና በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኩል ደግሞ የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ድሪባ ፈየራ መሆናቸው መግባባት ላይ ተደርሶ ርክክቡ ተደርጓል፡፡ ስለሆነም የተከበራችሁ አይነስውራን ዜጎች፣ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኩል ሊሻሻሉ ይገባል ወይም ሊታረሙ ይገባል የምትሏቸውን ጉዳዮች በአካል ወይም በዚህ የቴሌግራም ግሩፕ አማካኝነት ማቅረብ እንደምትችሉ እየገለጽን በዛሬው እለት ማኅበሩ የተረከባቸውን የድምጽ ውሳኔዎችን ከማኅበሩ የቴሌግራም ግሩፕ ወይም በአካል በመቅረብ አመቺ በሆነ መንገድ ከማኅበሩ የአይሲቲ ባለሙያ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Skip to content