የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር በትናንትናው እለት ማለትም፣ በቀን 22/10/2017 አመተ ምህረት በአዲስ አበባ በደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለብሬል ክፍል ሰራተኞቹና የብሬል ጽሁፍ የአርትኦት ስራ በመስራት የስራ ክፍሉን በበጎ ፈቃደኝነት ላገለገሉና እያገለገሉ ላሉ አባላቱ ስልጠና ሰጠ። ስልጠናው የማራካሽ ስምምነትን ለማስተዋወቅ ያለመ ሲሆን 51 ተሳታፊዎች ታድመውበታል።
ስልጠናውን የሰጡት በማራካሽ ስምምነት ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር ያደረጉት እንዲሁም ደግሞ የማራካሽ ስምምነትን በማርቀቅና በማስጸደቅ ዙሪያ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት ዶክተር ዮሀንስ ታከለ ናቸው። በስልጠናው የማራካሽ ስምምነት ምንነት፣ ለአይነ ስውራን ያለው ፋይዳ፣ ስምምነቱን ለማስፈጸም የሚረዳ ሀገርኛ አዋጅ ለማውጣት ያሉ ተግዳሮቶች፣ አዋጁን ለማስወጣት በሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ማህበርም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሊሰሩባቸው ስለሚገቡ የትኩረት ነጥቦችና ሌሎችም ጉዳዮች ተዳሰዋል።
ስልጠናው የተከናወነው በአፍሪካ አይነ ስውራን ህብረት በኩል ከስዊዲን አይነ ስውራን ማህበር በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን በመድረኩ የአፍሪካ አይነ ስውራን ህብረት ተጠባባቂ ዋና ስራ አስኪሃጅ ሚስተር አብርሃም ማቴታ በክብር እንግድነት ተገኝተው ስልጠናውን በመክፈቻ ንግግር አስጀምረዋል። ከሚስተር አብርሃም ማቴታ በተጨማሪ የማህበራችን ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንትን ጨምሮ 4 የቦርድ አባላትም ታድመዋል። በዶክተር ዮሃንስ የተዘጋጀው የስልጠና ክፍል ከተጠናቀቀ በኋላ የማህበራችን ፕሬዝዳንት አቶ አበራ ረታ የማራካሽ ስምምነትን ኢትዮጵያ እንድትፈርም ለማድረግ ማህበራችን የተጫወተውን ሚናና የነበረውን ውጣ ውረድ የሚያሳይ ገለጻ አድርገዋል። በመጨረሻም ከስልጠናው ተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥቆማዎች ከተሰጡ በኋላ የማህበራችን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ፋንታሁን መንግስቴ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ስልጠናው ተጠናቋል።
ስለ ማራካሽ ስምምነት ምንነትና ይዘት በጥልቀት ለማወቅ ከታች የተያያዘውንና ዶክተር ዮሃንስ ታከለ በAfrican Disability rights year book ላይ “The need Beyond Ratifying Marrakesh Treaty” በሚል ርእስ ያሳተሙትን ጥናታዊ ጽሁፍ ያንብቡ።


Leave a Reply