የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር የደብረ-ብርሃን እና አካባቢው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከካድር (Collective Action on Disability Rights) ፕሮጀክት ከሰብዓዊ መብትና ድርጅታዊ ልማት እና ኢኮኖሚ ልማት ክፍሎች ጋር በመተባበር ከሀምሌ አምስት እስከ ስድስት ለሁለት ቀናት በደብረ-ብርሃን ከተማ ትኩረቱን በአካል ጉዳተኞች የሰብዓዊ መብቶች መከበር ላይ ያደረገ የወርክሾፕ ፕሮግራም ተካሂዷል። በፕሮግራሙ ላይም ከማህበራዊ ጥበቃ ማስተባበሪያ፣ ከሲቪል ሰርቪስ፣ ከአደረጃጀት ዘርፍ፣ ከፖለቲካ ዘርፍ፣ ከሥራ አስፈጻሚ፣ ከመሰረተ-ልማት እና የተለያዩ ተቋማትን የወከሉ ቁልፍ የከተማ እና የክ/ከተማ ኃላፊዎች እና ቡድን መሪዎች፣ እንዲሁም የደብረ-ብርሃንና አካባቢው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴን ጨምሮ እዛው የሚገኙ የቦርድ እና የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።
በፕሮግራሙ ኢትዮጵያ ያጸደቀችው የተባበሩት መንግስታት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነትን ጨምሮ፣ ዘላቂ የልማት ግቦች፣ ሀገራዊ እና ክልላዊ ህጎች አፈጻጸም እና በክልሉ እና በከተማዋ አጠቃላይ የአካል ጉዳተኞችን መብቶች በተሟላ ደረጃ ለማስከበር እና ለማክበር የሚታዩ ተግዳሮቶች እና እምርታዎች ላይ ያተኮረ ገለጻ በባለሙያ ተደርጓል።
የቅርንጫፉ የሥራ አስፈጻሚ፣ የቦርድ እና የጠቅላላ ጉባዔ አባላትም በከተማዋ በዓይነስውራን የሥራ አጥነት፣ የተደራሽነት ችግሮች፣ የአካል ጉዳተኞች በአመራር ደረጃ ቦታ ያለማግኘት፣ተደራጅቶ የሥራ ቦታ ማግኘት ላይ የሚታዩ ክፍተቶች፣ የረዳት አለመቀጠርን ጨምሮ ሌሎች ምክንያታዊ ማመቻቸቶች (Reasonable Accommodations) አለመኖራቸው፣ በሥራ ቦታ ዝውውር ላይ የሚታዩ ችግሮች፣ በትምህርት እና ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከአካል ጉዳተኞች አንጻር የሚታዩ ክፍተቶችን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎችን ለፕሮግራሙ ተሳታፊ አመራሮች በተደራጀ መልኩ አቅርበዋል።
በወርክሾፑ ላይም በከተማው የዓይነስውራን ብሎም የሌሎች አካል ጉዳተኞችን ችግሮች ለመቅረፍ የሚታዩ ጅምር ሥራዎች አበረታች መሆናቸው እና ለዚህም የከተማ እና የክ/ከተማ አመራሮች መመስገን እንዳለባቸው በተለይም በጠባሴ ክ/ከተማ የሚሠሩ ሥራዎችን እውቅና መስጠት እንደሚያስፈልግ እና ሌሎችም ክ/ከተሞች እንደ ሞዴል ወስደው ሊሠሩ እንደሚገባ ተነስቷል። ነገር ግን በአጠቃላይ በከተማዋ ዓይነስውራንን ጨምሮ ሌሎች አካል ጉዳተኞች የተለያዩ ሰብዓዊ መብቶቻቸው በተሟላ ደረጃ ተከብረውላቸው የኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና የመሥረተ-ልማት አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታቅዶ መሠራት እንደሚገባ እና ለተግባራዊነቱም በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ኃሳብ ቀርቦ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎ ከስምምነት ላይ መድረስ ተችሏል።


Leave a Reply