የወላይታ ሶዶ አይነ ስውራን ት/ቤት


አጭር ታሪክ

የወላይታ ሶዶ አይነ ስውራን ት/ቤት በቀድሞው የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት በወላይታ  ኣውራጃ በወላይታ ሶዶ ከተማ የአካባቢውን ዓይነስውራን ህጻናትን የእጅ ስራ ስልጠና [vocational training]እና የዘመናዊ ትምህርት እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ የተመሰረተ እና ለትርፍ ያልተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ ትምህርት ቤት ነበር።
ይህ በአይነቱ ልዩ የሆነ የዓይነስውራን ት/ቤት እንደግሪጎሪያኑ የዘመን ዓቆጣጠር  በመስከረም 1964 ዓ/ም /Sudanese Interior Mission [SIM]/ ተብሎ ይጠራ በነበረው ሀገር በቀል ያልሆነ የሚሲዮናዊያን ቡድን ኣማካኝነት የተቋቋመ ትምህርት ቤት ነው። ለተቋሙ መመስረት ምክንያት የነበረው እነዚህ ሚሲዮናዊያን የሶዶ ክርስቲያን ኣካዳሚ ብለው ባቋቋሙት ት/ቤት ውስጥ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ዓይናማ ተማሪዎች የአራተኛ ክፍል ትምህርት ሲያጠናቅቁ ለ1 ዓመት ገጠር ኣካባቢ ወደ ሚገኙ የቃለህይወት አብያተክርስቲያናት እየተላኩ ህጻናትን እንዲያስተምሩ የሚደረግበት መደበኛ ፕሮግራም ነበራቸው። ታዲያ እነዚህ ኣይናማ ተማሪዎች በተደጋጋሚ ሲያጋጥማቸው የነበረው አይነስውራን ህጻናትም ከዓይናማ ጓደኞቻቸው ጋር እየተቀላቀሉ የኣካዳሚው ተማሪዎች የሚሰጡትን ትምህርት በቃል ሲከታተሉ ያዩ እና ሁኔታውን ለሚሲዮናዊያኑ ያስረዳሉ። በተጨማሪም ዓይነስውራን ህጻናት የነበራቸውን የትምህርት ጉጉት ብቻም ሳይሆን በትምህርት አቀባበላቸውም ከሌሎቹ ኣይናማ ጓደኞቻቸው በብዙ የሚልቁ መሆናቸውን ማስተዋል እንደቻሉ በዝርዝር ያቀርባሉ። ሚሲዮናዊያኑም በተደጋጋሚ ሲቀርብላቸው የነበረውን ጥያቄ ለመመለስ ሲሉ ይህንን ታሪካዊ ትምህርት ቤት ለመክፈት እና ስራ ለማስጀመር ቻሉ።
ይህ አዲስ ተቋም ስራውን ሲጀምር በአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ስምንት ወንድ ልጆችን ይዞ ሲሆን የተማሪዎቹ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መጥቶ በሶስት ኣመት ውስጥም 10 ልጃገረዶች  እና 40 ወንዶች በድምሩም 50 ሊደርስ የቻለውም በየአብያተ ክርስቲያናት በሚሰጠው የወንጌል ትምህርት ጋር ይሰጥ በነበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ዓይነስውር ልጆቻቸውን ደብቀው የነበሩትን ወላጆች ለማሳመን በተደረገ ከፍተኛ ቅስቀሳ ነበር። በዚያን ዘመን አይነስውርነት ከእርግማን እና ከ እርኩስ መንፈስ ጋር ተያይዞ የሚታሰብ በመሆኑ በርካታ የአካል ጉዳተኛ ልጆች ያሏቸው ወላጆች በነበረባቸው የግንዛቤ እጥረት የአካል ጉዳት ያለባቸውን ልጆች ሰው እንዳያይባቸው በጓዳ የመደበቅ ልማድ በኢትዮጵያ በስፋት የሚስተዋል ችግር ነበር።
በወቅቱ በትምህርት ቤቱ ከመደበኛ የቀለም ትምህርት በተጓዳኝ የተለያዩ የሞያ ትምህርቶችም ተማሪዎቹ እንዲከታተሉ ሲደረግ ቆይቷል። ሆኖም በወቅቱ የትምህርት ቤቱ መስራች እና Director የነበሩት ካናዳዊቷ ሚስ ኤልነር ኔውፈልድ የአይነስውራንን ትምህርት በሚመለከት ሲከተሉት ከቆየው የተለየ አዲስ ሀሳብ አመነጩ። ይህም አዲስ ኣቅጣጫ አይነስውራን የዳሰሳ ጽሁፍ [Braille] ጽህፈት እና ንባብ ከቻሉ በኋላ በቀለም ትምህርት በመቀጠል ፋንታ የእጅ ስራ ስልጠና ተሰጥቷቸው ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ማድረግ የሚል ነበር። በዚህ የሚሲዮናዊያን አዲስ መመሪያ ያልተደሰቱ አይነስውራን ተማሪዎች ለትምህርት ቤቱ ሀላፊዎች የሚያመርቷቸው የእጅ ስራ ውጤቶች አትራፊ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ለማሳመን እና በቀለም ትምህርቱ ለመቀጠል ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ቢያስረዷቸውም በሚሲዮናዊያን ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኙ ኣልቻሉም። ይባስ ብሎም እነዚሁ የት/ቤቱ ኣመራሮች የእጅ ስራ ትምህርት መምህራንን ቀጥረው በግድ እንዲማሩ ማድረጉን ቀጥለውበት አይነስውራኑ ተማሪዎች የአራተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ለእጅ ስራው የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁሶች ገዝተውላቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው ሄደው እንዲተዳደሩበት ሲደረግ ቆይቷል።
በዚህ መልክ እስከ እ.አ.አ 1975 ዓ/ም ድረስ ት/ቤቱ ስራውን ቀጥሎ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ፖለቲካዊ አብዮት ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጣው መንግስት በሚከተለው ከቀድሞው የተለየ ርእዮተ ዓለም ስጋት የገባቸው የውጪ ሀገር ዜጎች ጓዛቸውን ጠቅልለው  በወጡበት ወቅት የትምህርት ቤቱ አስተዳደሮችም ከኢትዮጵያ ሲወጡ ትምህርት ቤቱ ለመዘጋት በመገደዱ 127 አይነስውራን ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታቸው ላይ ለመፈናቀል እና ለመበተን ተዳርገዋል። በትምህርት ቤቱ መከፈት እና በጀመሩት የትምህርት ጣእም ከፍተኛ ደስታ ውስጥ ለነበሩት ኣይነስውራን ተማሪዎች ኣስደንጋጭ ክስተት ሆነ። በዚህም ሳቢያ የተስፋ ጭላንጭል ማየት ጀምረው የነበሩት አይነስውራን ተማሪዎች እጣ ፋንታቸው ወደተስፋ አልባው  የጎዳና ህይወት የመመለስ ኣደጋ ከፊታቸው ተጋረጠ። ለኣካባቢው ህብረተሰብም ሆነ ለሀገሪቱ ተስፋ የነበረው ተቋም ብዙም ሳይቆይ “ያገባኛል” ብሎ እንደራሱ ንብረት የሚጠብቀው  አካል በማጣት በርካታ ንብረቶቹ እንዳይዘረፉ በወቅቱ የወላይታ ኣውራጃ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ስምኦን ጋሎሬ በሰጡት ትእዛዝ መሰረት በኣካባቢው የሚገኘው የቀበሌ መስተዳድር እና የሶዶ ሆስፒታል በጋራ እንዲጠብቁት ሲደረግ እንደቆየ በወቅቱ በኣካባቢው ከነበሩ ነዋሪዎች መረዳት ተችሏል። ተቋሞቹም የተጣለባቸውን ሀላፊነት በሚገባ የተወጡ በመሆናቸው ምስጋና ይገባቸዋል።
በዚህ ሁኔታ ለአራት ዓመታት ተዘግቶ ከከረመ በኋላ ትምህርት ቤቱን የሚመለከት አዲስ የብስራት ዜና ተሰማ። ይኸውም በወቅቱ ከነበረው መንግስት በተለይም ከህዝባዊ ኑሮ እድገት ሚኒስቴር ጋር ሰፊ ውይይት እና ድርድር በማካሄድ ተቋሙን በቀድሞ ስሙ የእውራን ተራድኦ ህብረት ድርጅት ተብሎ የሚጠራው የአሁኑ የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሄራዊ ማህበር የጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤት በመሆኑ እንዲረከበው እና እንዲያስተዳድረው ከስምምነት ላይ በመደረሱ ትምህርት ቤቱ “የወላይታ የትምህርት እና የምርት ማእከል” በሚል ስም እ.አ.አ በ1979 ዓ/ም በድጋሚ ለመከፈት እና አገልግሎት ለመስጠት በቃ። በት/ቤቱ ዳግም መከፈት እና አገልግሎት መስጠት በጊዜው በነበረው የመገናኛ ዘዴዎች እጥረት ሳቢያ ጥረቶቻቸውን ማቀናጀት ባይችሉም በወቅቱ የትምህርትን ፋይዳ የተረዱ በወላይታ ኣካባቢ የሚኖሩ ዓይነስውራን ተማሪዎች እና የሰበታ መርሀእውራን ት/ቤት ተማሪዎች ት/ቤቱ ተዘግቶ እንዳይቀር በእየአካባቢያቸው ሲያደርጉት የነበረው ያላሰለሰ ጥረት በቀላሉ የሚታይ እንዳልነበረ ከቀድሞ የወላይታ ሶዶ ዓይነስውራን ት/ቤት ተማሪዎች መረዳት ይቻላል።
የሆነው ሆኖ ተጠቃሹ ማህበር ትምህርት ቤቱን ለማስተዳደር በቂ የገንዘብ አቅም ስላልነ በረው ረዳት ማፈላለግ ነበረበት። በዚህም ሂደት መሰረቱን በጀርመን ሀገር ያደረገ Christian Blind Mission [CBM] የተባለ አለም ኣቀፍ ምግባረሰናይ ድርጅት ተገኘ። ይህም የበጎ አድራጎት ድርጅት እንደኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች ውስጥ የሚኖሩ አካል ጉዳተኛ ዜጎች የሚደርስባቸውን ከማህበራዊ ኑሮ መገለል እና ኢኮኖሚያዊ አድሎ ለማስቀረት የትምህርት፣ የስልጠና እና የማቋቋም ፕሮግራሞችን ቀርጾ በኢትዮጵያ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት በጣት ከሚቆጠሩ ድርጅቶች አንዱ ነበር። በዚህም እንቅስቃሴው CBM ለሶስት አስርት አመታት ለትምህርት ቤቱ ብቸኛ የበጀት ምንጭ ሆኖ ዘልቋል።
ታዲያ በዚህ ጊዜ ትምህርት ቤቱ በወላይታ አካባቢ ላይ ተወስኖ የነበረው የተማሪ ቅበላ አቅሙን ማሳደግ ላይ ብቻ ሳይወሰን ከሁሉም የሀገራችን ክፍሎችበዓይነስውርነታቸው ምክንያት እንደ እድሜ አቻዎቻቸው አይናማ ልጆች የመማር እድል ተነፍጓቸው እና በእየወላጆቻቸው ጓዳ ተደብቀው እና ለአስከፊው የልመና ህይወት ተዳርገው  የነበሩ ህጻናት ጭምር በዘመቻ መልክ በብዛት ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ ለማድረግ ተችሏል።
ከታሪኩ መገንዘብ እንደሚቻለው ይህ ትምህርት ቤት በመደበኛነት ከሚሰጣቸው የቀለም ትምህርቶች ባሻገር በስርኣተ ትምህርቱ ውስጥ ተካቶ ይሰጥ በነበረው የእርሻ፣ የሽመና፣ የእጅ ስራ፣ የኑሮ በዘዴ፣ የሙዚቃ እና የመሳሰሉ የትምህርት ኣይነቶችን ተጠቅመው ኣይነስውራን ተማሪዎች ክህሎቶቻቸውን እና ተሰጥዎቻቸውን እንዲያዳብሩ ሲያግዝ ቆይቷል።
ቀስ በቀስም ትምህርት ቤቱ በገቢ ከጥገኝነት ተላቅቆ ራሱን እንዲችል በተደረገው እንቅስቃሴ ኣይነስውራን ሊሰሯቸው የሚችሏቸው ፕሮጀክቶች ቀርጾ ተግባራዊ ለማድረግ ተሞክሮም ነበር። ከእነዚህም ፕሮጀክቶች
ውስጥ የጓሮ አትክልት ልማት፣ የዶሮ እርባታ፣ የወተት ከብቶች ልማት፣ የጠመኔ እና ሳሙና  ምርት የሸክላጡብ እና የብሎኬት ምርቶች ጥቂቶቹ ነበሩ። ይሁን እንጂ በአይነስውራን የሚመረቱት እነዚህ እቃዎች በባለሞያዎች ክትትል ማነስ፣  በተፈላጊ ጥሬ እቃዎች እና በገበያ እጦት እና በመሳሰሉ ችግሮች ምክንያት ፕሮጀክቶቹ በታሰበው ደረጃ ብዙም ሊራመዱ ኣልቻሉም። ይህ ማለት አይነስውራን የሚያመርቷቸው ነገሮች ተፈላጊ አይደሉም ማለት ሳይሆን ተገቢው ትኩረት ቢሰጠው ኖሮ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረብ የሚችሉ ምርቶችን ማምረት እንደሚችሉ ሊሰመርበት እንደሚገባ ለመጠቆም ነው። በመሆኑም ዛሬ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ በቀለም ትምህርት ገፍተው መሄድ ያልቻሉ አይነስውራን ዜጎች ከት/ቤቱ በቀሰሙት የእጅ ስራ ጥበብ ብሎኬት፣ የሸክላ ጡብ፣ የሽመና ውጤቶች እና ሌሎችንም ስራዎች በመስራት ለመተዳደሪያነት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ትምህርት ቤቱ በኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሄራዊ ማህበር ስር ሆኖ ከCBM በሚያገኘው ፈንድ  ተጠቅሞ ሁሉን  ዓቀፍ እንክብካቤ እያደረገ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ 6ኛ ክፍል በአዳሪነት ከሚሲዮናዊያኑ በተሻለ ኣያያዝ በማስተማር ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ ሲያልፉም ቀደም ሲል በከፍተኛ ችግር ውስጥ ሆነው የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ይማሩ የነበረ ሲሆን ከ1997 ዓ/ም ጀምሮ ግን ተቋሙ ለክልሉ መንግስት ሲያቀርብ የቆየውን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ትምህርታቸውን በመንግስት የሚመደብላቸው የኪስ ገንዘብ [stipend] ታግዘው ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን በኣጎራባች የመንግስት ትምህርት ቤቶች እንዲቀጥሉ ለማድረግ ተችሏል። በኋላም ምንም እንኳን ኣስቀድሞ እንደታሰበው ዘለቄታዊ ማድረግ ባይቻልም ተጨማሪ መማሪያ ክፍሎችን በመገንባት የሰባተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ዓይነስውራን ተማሪዎች በተመላላሽነት በትምህርት ቤቱ ለተወሰኑ ዓመታት እንዲማሩ ሲደረግም ነበር። በሌላ በኩል ከአካባቢው ነዋሪ ማህበረሰብ በተደጋጋሚ ሲቀርብለት የነበረውን ጥያቄ ለመመለስ በተደረገ ጥረት በዘርፉ በሚገባ የሰለጠኑ ባለሞያዎችን መድቦ ደረጃውን የጠበቀ የአጸደ ህጻናት ትምህርት ኣገልግሎት በተጠናከረ ሁኔታ በአካባቢው ለሚኖሩ እና ከፍለው መማር ለማይችሉ ዓይናማ ህጻናት በነጻ ሲሰጥም ቆይቷል። በዚህም ተግባሩ በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ ተቋሙ ያለው ተቀባይነት ከፍ እንዲል ከማስቻሉም ባሻገር የኢ/ፌ/ዲ/ሪ መንግስት ባወጣው የትምህርት እና የስልጠና ፖሊሲ ውስጥ ያካተተው የአካቶ ትምህርት [Inclusive Education] መርሀግብር በትምህርት ቤቱ በተወሰነ መልክም ቢሆን ቀደም ብሎ መጀመሩን መገንዘብ ይቻላል።
ይህ አንጋፋ ት/ቤት መልካም ራእይ ኣንግቦ የተነሳ እና በስኬት የቆየ ቢሆንም በኢትዮጵያ ሚሊኒየም መባቻ ገደማ የተለያዩ ችግሮች ኣጋጥመውትም ነበር። የረጂው ድርጅት ማለትም የCBM ድጋፍ ማቋረጥን ተከትሎ ተቋሙ በድንገት የተከሰተበት የበጀት እጦት የመዘጋት አፋፍ ላይ አድርሶትም ነበር። ሆኖም ምስጋና ለደቡብ ክልላዊ መስተዳድር እና ለወላይታ ዞን አስተዳደር  ያንን ኣስቸጋሪ ወቅት ለመሻገር የሚያስችል ለአምስት ወራት በጀት የሚሆን 348000 ብር በመደጎም ያላቸውን አጋርነት በተግባር አሳይተዋል። በዚህም ጊዜያዊ ድጋፍ ተማሪዎቻችንን ከመበተን ከመታደጉም በተጨማሪ ለትምህርት ቤቱ መምህራን እና ሰራተኞችም በጊዜያዊነት “እፎይ” እንዲሉ አስችሎ ነበር። ይህ ችግር ት/ቤቱን ሊያጋጥም የቻለው ለ3 አስርት አመታት በበጀት ሲደግፍ የቆየው አለማቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት ሳይጠበቅ የፖሊሲ ለውጥ በማድረጉ እና የኢትዮጵያ መንግስትም በደነገገው የበጎ ኣድራጎት ድርጅቶች እና የሲቪል ማህበራትን በሚመለከተው አዋጅ መሰረት የት/ቤቱ ባለንብረት የሆነው የኢትዮጵያ አይነስውራን ብሄራዊ ማህበር ኢትዮጵያዊ ማህበር ሆኖ በመመዝገቡ ትምህርት ቤቱ የውጪ ደጋፊ በማጣቱ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ለችግሩ መቀረፍ የትምህርት ቤቱ መምህራን እና ሰራተኞች ተቋሙ እንዳይዘጋ እና ለስራ ኣጥነት እንዳይዳረጉ ብቻም ሳይሆን ትምህርት የጀመሩ አይነስውራን ህጻናት ወደ ጎዳና እንዳይበተኑ በአካባቢያቸው እና በክልላቸው ውስጥ ሲያደርጉት ከነበረው  የመፍትሄ ማፈላለግ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሄራዊ ማህበርም በበኩሉ በፌደራል ደረጃ ሲያደርግ የቆየው እልህ ኣስጨራሽ ጥረት ፍሬ አፍርቶ ጊዜያዊ መፍትሄ ለማግኘት ተችሏል። ይኸውም ቀደም ሲል ት/ቤቱን በበጀት ሲደግፍ የቆየው CBM፣ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት/ቢሮ፣ የወላይታ ሶዶ ኣይነስውራን ት/ቤት፣ ኢ/አ/ብ/ማ እና ትምህርት ሚኒስቴር አባል የሆኑበት ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሂደቱን እንዲከታተል እና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያፈላልግ እስከዚያውም CBM ድጋፉን እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር። በዚህም መሰረት ለ2 ዓመታት CBM በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ይሰጥ በነበረው ድጋፍ ከቆየ በኋላ ለዘላቂው መፍትሄ ምንም ኣይነት ኣቅጣጫ ኮሚቴው ማስቀመጥ ሳይችል ቀርቷል። በዚህም ችግር ሳቢያ ትምህርት ቤቱ በ2013 በተገቢው ወቅት ሳይከፈት ለመቆየት ተገድዷል። ሆኖም ለ7 ወራት አገልግሎት ሳይሰጥ የቆየው ተቋም በድጋሚ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች አማካኝነት ከሌላ ኣለም ኣቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት ለአንድ ዓመት በተገኘው ፈንድ አማካኝነት ስራው ሳይስተጓጎል ለማስቀጠል ጠቅሞታል። በዚህ ከUSA AID ከተባለው ድርጅት በተለገሰው 1.2 ሚሊዮን ብር ዘግይቶም ቢሆን ተማሪዎቹን ለእረፍት ከሄዱበት በማሰባሰብ  መጋቢት 2014 ትምህርት ለማስጀመር ተችሏል። ሆኖም “ሳይደግስ አይጣላም” እንዲሉ በዚሁ ዓመት ት/ ቤቱ እና የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሄራዊ ማህበር ለተለያዩ ድርጅቶች በበተኑት ደብዳቤ አማካኝነት የድጋፍ ጥያቄ በማቅረብ ችግሩን በዘላቂነት የሚያስወግድ መፍትሄ ለማግኘት በተደረገ እልህ ኣስጨራሽ ጥረት ውስጥ Beloved Ethiopia ከተሰኘ በወላጅ አጥ ህጻናት ላይ በትኩረት የሚሰራ ሀገር በቀል ምግባረ ሰናይ ድርጅት ጋር የስራ ግንኙነት ይፈጠራል።
ይህም ግንኙነት በኢ/አ/ብ/ማ እና በድርጅቱ መካከል በተደጋጋሚ በተደረጉ ውይይቶች ዳብሮ እና ጎልብቶ ወደ ስምምነት ኣመራ። በዚህም ስምምነት መሰረት Beloved Ethiopia ከseptember 2014 ጀምሮ ሲያደርግለት በቆየው ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ ኣማካኝነት የትምህርት ስራው ሳይስተጓጎል ላለፉት ኣራት ዓመታት ለማስቀጠል ተችሏል። ነገር ግን ት/ቤቱ እስከ 8ኛ ክፍል ሲያስተምር የነበረውን ማስቀጠል እንዳልተቻለ እና በአሁኑ ወቅት እስከ 4ኛ ክፍል ላሉት ተማሪዎች ብቻ እየሰጠ ሲሆን 150እና ከዚያ በላይ ለሚሆኑ  ትምህርታቸውን በአዳሪነት ለሚማሩ ዓይነስውራን ተማሪዎች አገልግሎት መስጠት እየቻለ በሚያገኘው የድጋፍ በጀት ውስንነት ሳቢያ አገልግሎቱን ከ60 ላልበለጡ ተማሪዎች ብቻ በመስጠት ላይ ይገኛል። ጉዳዩን ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ኣሁን ተቋሙ ባለበት ሁኔታ ስለቀጣይ የት/ቤቱ እጣ ፋንታ በግልጽ ሊታወቅ አለመቻሉ ነው።
በሌላ በኩል የወላይታ ሶዶ ዓይነስውራን ት/ቤት መምህራንም ሆኑ ሌሎቹ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የተሞክሮ እና የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት በሶዶ ከተማ ከሚገኙ ት/ቤቶች ጋር በክላስተር ታቅፎ በንቃት ተሳትፎውንም ሲያሳይ ቆይቷል። በዚሁ እንቅስቃሴ በአካባቢው ብቻ ሳይወሰን እ.አ.አ በ 1998 ዓ/ም በተጀመረው በሀገር ኣቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ዓይነስውራንን በሚያስተምሩ ት/ቤቶች መካከል በየዓመቱ በሚደረግ የእስፖርት እና የቀለም ውድድር ላይም በመሳተፍ አኩሪ ታሪኮችን ሲያስመዘግብ ቆይቷል። ከዚህም በተጨማሪ ት/ቤቱ የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሄራዊ ማህበር ከተረከበው ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በአብዛኛው በኣይነስውራን ሀላፊዎች ሲመራ መቆየቱ ለሌሎችም መሰል ተቋሞች በአርአያነት ሊታይ የሚገባው ነው።
በአጠቃላይ የወላይታ ሶዶ አይነስውራን ት/ቤት ሲሰጥ ከቆየው አገልግሎት አንጻር ምንም ያልተዘመረለት ብቻም ሳይሆን በመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚገባውን ያህል ትኩረት ያላገኘ ተቋም ሆኖ ይታያል። ይህም ሲባል ተቋሙ ባሳለፈውከ50 ዓመታት በላይ ቆይታው በቁጥር ከ2000 በላይ ዓይነስውራን ዜጎች በስነምግባር እና በእውቀት አንጾ በማሳደጉ በዲፕሎማ፣ በመጀመሪያ ድግሪ፣ በማስትሬት እና በዶክትሬት ደረጃ የተመረቁ የህግ፣ የማህበረሰብ ጥናት፣ የትምህርት ባለሞያነት እና በሌሎችም የስራ መስኮች ተሰማርተው የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ሀላፊነት  በመወጣት ላይ ይገኛሉ። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ስር ብቻ ወደ 120 የሚደርሱ በዚህ ት/ቤት ተምረው ያለፉ ዓይነስውራን መምህራን እየሰሩ መሆኑን በማስረጃነት ማቅረብ ይቻላል።
ስለሆነም ከላይ ከቀረበው አጭር የትምህርት ቤቱ ታሪክ መረዳት የሚቻለው
  1. ተቋሙ በዘርፉ የካበተ ልምድ ባለቤት መሆኑ
  2. ዓይነስውራን ትንሽ ድጋፍ ካገኙ ምርታማ መሆናቸውን ማሳያ እንደሆነ
  3. ተቋሙ ከየትኛውም ባለድርሻ ኣካል ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን
  4. ለተቋሙ ህልውና መጠበቅ የአካባቢው ህብረተሰብ እና መንግስታዊ ተቋማት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸው እና ወደፊትም እንደሚኖራቸው
  5. በአብዛኛው ዓይነስውራን የሚመጡት እንደመንገድ፣ ትምህርት ቤቶች ያሉ መሰረተልማቶች ተሟልተው ከማይገኙበት አካባቢዎች በመሆኑ ት/ቤቱ በአዳሪነት የትምህርት አገልግሎት መስጠቱ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን
  6. ት/ቤቱ በተለይም በአካቶ ትምህርት ዙሪያ የትምህርት መረጃ ማእከል [Resource centre] ሆኖ ሊያገለግል የሚችል መሆኑ
  7. ተቋሙበበጀት ራሱን አለመቻሉ በተደጋጋሚ ህልውናውን የሚፈታተን መሆኑን በተለይም ካለፉት 10 ዓመታት ወዲህ ያጋጠመው የፈንድ እጥረት የሚሰጠውን የትምህርት ደረጃ ከ8ኛ ክፍል ወደ 4ኛ ክፍል ዝቅ ለማድረግ መገደዱን
  8. ት/ቤቱ በክልላችን በአይነቱ ብቸኛ መሆኑን እና ልዩ ትኩረት እንደሚያሻው
  9. በሚከፈላቸው ደምወዝ አነስተኛነት ብዙ መምህራን ስራ ሲለቁ በምትካቸው ለመቅጠር የት/ቤቱ የበጀት አቅም የማይፈቅድ በመሆኑ ባሉት መምህራን ላይ ጫና ከመብዛቱ በላይ የትምህርት ጥራቱ እየተጓደለ መምጣቱን
  10. ላሉትም መምህራን እና ሰራተኞች የሚከፈላቸው ደምወዝ ከወቅቱ የኑሮ ውድነት ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ መሆኑን እና የሰራተኞችን የስራ ተነሳሽነት ስሜት እየጎዳ መሆኑ
  11. ተቃቋሙ በተፈጠረበት የበጀት እጥረት ሳቢያ በየዓመቱ የሚቀበላቸው ጀማሪ ዓይነ ስውራን ተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቶ ከአስር በታች መድረሱ
  12. ተማሪዎቹ ራሳቸውን ሊያስተዳድሩ በማይችሉበት እድሜያቸው ከት/ቤቱ እንዲወጡ እና የ5ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በመንግስት በሚመደብላቸው የኪስ ገንዘብ ኣማካኝነት ለመቀጠል እየተቸገሩ መሆኑ
ባለበት የበጀት እጥረት ምክንያት ተቋሙ ወደ Braille የተገለበጡ ወቅታዊ የመማሪያ እና የማጣቀሻ መጻህፍት እጥረት በሚሰጠው ትምህርት ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ መሆኑ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Skip to content