የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ከካድር ፕሮጀክት (Collective Action on Disability Rights) ፈጻሚ አካል ከሆነው ከፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውሱንነት ብሔራዊ ማኅበር ጋር በመተባበር ሀምሌ 25 እና 26 ለሁለት ቀናት ከባህርዳር ከተማ ከስድስቱም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ቤተሰቦች ተሳታፊ የሆኑበት ለአካል ጉዳተኛ ልጆች ወላጅ እና አሳዳጊዎች መሰረታዊ በሆኑ የአካል ጉዳተኞች መብቶች፣ በአስተዳደግ እና በድጋፍ አሰጣጥ ላይ ያተኮረ ስልጠና መስጠት ተችሏል።
የስልጠናው ዓላማም ወላጆችና አሳዳጊዎች አካል ጉዳተኛ ልጆች ስለሚሰጣቸው ድጋፍ እና ክብካቤ በማወቅ ለልጆቹ የተሟላ እድገት ግዴታቸውን እንዲወጡ እና የአካል ጉዳተኛ ልጆችን መብት አውቀው ለመብቶቹ መከበርም እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል ነው።
የስልጠናው ተካፋይ ወላጅ እና አሳዳጊዎች ልጆቻቸውን በተመለከተ ስለሚገጥሟቸው የመብት ጥሰቶች አንስተው በምሬት ተናግረዋል። የአንዳንድ ትምህርት ቤቶች አካል ጉዳተ ያለባቸውን ተማሪዎች አለመቀበል፣ እንዲሁም የአንዳንድ መምህራን አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ለማስተማር ፍላጎት ማጣት፣ ትራንስፖርትንና ጤናን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን ፍትሓዊ በሆነ መልኩ ለማግኘት የሚገጥሙ ተግዳሮቶች እና በማህበረሰቡ ውስጥ ስለአካል ጉዳተኝነት ያለው ዝቅተኛ ግንዛቤ የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ካነሷቸው አንኳር አንኳር ችግሮች መካከል ይገኙበታል።
የበዙ ወላጆች እና አሳዳጊዎች ህጻናት አካል ጉዳተኞች ስለሚገጥሟቸው የትምህርት ችግሮች አበክረው የተናገሩ ሲሆን፣ በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የክልሉ የትምህርት ቢሮ እና የከተማው የትምህርት መመሪያ ኃላፊዎች ለሁሉም አካል ጉዳተኛ ተደራሽ የሆነ ትምህርት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ ዓይነስወራን ብሔራዊ ማኅበር ጋር የተሠሩ ሥራዎች አካቶን በተሟላ ደረጃ ለማምጣት የሚያስችሉ እንደሆኑ አንስተዋል። አክለውም፣ አካል ጉዳተኛ ተማሪ የማይቀበሉ ትምህርት ቤቶችን እንዲሁም አካል ጉዳተኛን አንቀበልም አናስተምርም የሚል አካል ካጋጠማቸው ጥቆማ መስጠት እንደሚችሉ ለተሳታፊዎች ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በፕሮግራሙ የአካል ጉዳተኛ ልጆች ወላጅና አሳዳጊዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች በተመለከተ ለልጆቻቸው ውትወታ በማድረግ ጥብቅና እንዲቆሙ፣ ከአካል ጉዳተኛ ማህበራት ጋር እንዲሠሩ፣ ተስፋ ሳይቆርጡ ታሪካቸውን በማካፈል ለሌሎች ወላጅ እና አሳዳጊዎች ምሳሌ በመሆን
የተደበቁ አካል ጉዳተኛ ልጆች ወደ አደባባይ ወጥተው ለትምህርት እንዲበቁ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እና ልጆቻቸው መብት ያላቸው ዜጎች እንጂ ሸክም እንዳልሆኑ ማወቅ እንዳለባቸው በመድረኩ ላይ ተነስቷል።
ፕሮግራሙም የአካል ጉዳተኛ ልጆችን መብቶች በተሟላ ደረጃ በማስከበሩ ረገድ ግንዛቤ የሚፈጥር እና ለተግባር የሚያነሳሳ መልካም ጅማሮ እንደሆነ ከተሳታፊዎች ተነስቷል።

Leave a Reply