በትግራይ ክልል የካድር ፕሮጀክት የማስጀመሪያ ስነ ስርአት ተካሄደ።


የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር ከኖርዌ አይነ ስውራንና ከፊል እይታ ያላቸው ማህበር በተደረገለት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ Collective Action for Disability Rights (CADiR) የተሰኘ ፕሮጀክት እየተገበረ መሆኑ ይታወቃል። ቀደም ሲል በተለያዩ አካባቢዎች ፕሮጀክቱን በይፋ የማስጀመር ስነ ስርአት የተከናወነ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ተራው የትግራይ ክልል ሆኗል። በዛሬው እለት ማለትም ሀምሌ 15 ቀን 2017 በመቀሌ ከተማ ዘማሪያስ ሆቴል የትግራይ ክልል ማህበራዊ ጉዳይና መልሶ ማቋቋም ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ገብረ ስላሴ ታረቀኝ፣ የማህበራችን የቦርድ አባል አቶ ሀብቱ ካሳይ፣ የማህበራችን የጠቅላላ ጉባኤ ጸሀፊ አቶ ሀይለ ልኡል ምስጋናው፣ የካድር ፕሮጀክት የኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ግዛቸው፣ የማህበራችን የመቀሌ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገብረኪዳን ሀዱሽ፣ የአክሱምና የመቀሌ አካባቢ ተመራጭ የማህበራችን የጠቅላላ ጉባኤ አባላት፣ ከልዩ ልዩ የትግራይ ክልል መንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ ተወካዮች፣ የአይደር ትምህርት ቤት መምህራን፣ የካድር ፕሮጀክት አስተባባሪዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው 70 ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት የፕሮጀክቱ የመክፈቻ ስነ ስርአት ተከናውኗል።
የመክፈቻ ስነ ስርአቱን በእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስጀመሩት አቶ ገብረኪዳን ሀዱሽ፣ የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር ከዚህ ፕሮጀክት ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ENAB RISING የተሰኘ ፕሮጀክት መተግበር መጀመሩን አስታውሰው አሁን ደግሞ ማህበሩ CADiR የሚል ስያሜ ያለው ተጨማሪ ፕሮጀክት ለመተግበር ወደ ትግራይ ክልል መምጣቱ በትግራይ ውስጥ ላሉ አካል ጉዳተኞች በተለይም ለአይነ ስውራን በጣም ጠቃሚ ነው ብለዋል። ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት ከትግራይ ክልል መንግስታዊ ተቋማትና መንግስታዊ ካልሆኑ ባለ ድርሻ አካላት ጠንካራ ስራ የሚጠበቅ መሆኑን አሳስበው የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ስነ ስርአቱን በይፋ እንዲከፍቱ የክልሉ ማህበራዊ ጉዳይና መልሶ ማቋቋም ምክትል ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ገብረ ስላሴ ታረቀኝን ጋብዘዋል።
አቶ ገብረ ስላሴ ታረቀኝ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በትግራይ ክልል ውስጥ በርካታ አካል ጉዳተኞች የመኖራቸውን ያህል አካል ጉዳተኞችን ትኩረት አድርገው የሚሰሩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች እንብዛም የሌሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። በክልሉ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን ተጨባጭ ችግሮች በስፋት ያብራሩት ምክትል ቢሮ ሀላፊው፣ ማህበሩ የበኩሉን ሀላፊነት ለመወጣት ፕሮጀክት ነድፎ ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ክልሉ መምጣቱን አድንቀዋል። በመጨረሻም ክልሉ ማህበሩን ማገዝ ባለበት ሁኔታ ሁሉ ለማገዝ ያለውን ዝግጁነት በመግለጽ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ስነ ስርአቱን ከፍተዋል።
ፕሮግራሙ በይፋ ከተከፈተ በኋላ የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ሀብቱ ካሳይ፣ የማህበሩን ፕሬዝዳንት በመወከል ለፕሮግራሙ ታዳሚ ቁልፍ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ማህበሩ ለበርካታ ጊዜያት በትግራይ ክልል የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ለማፈላለግ ሲሞክር የቆየ ቢሆንም በነበረው የጸጥታ ችግር ምክኒያት ለጋሽ አካላት በክልሉ ለሚደረጉ የፕሮጀክት ሀሳቦች ዝግ እንደነበሩ አስታውሰዋል። ይሁንና ማህበሩ ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት ዛሬ እየተከፈተ ያለውን ፕሮጀክት ወደ ትግራይ ክልልም ማምጣት መቻሉን አስረድተዋል። ፕሮጀክቱ ሰሜናዊት ኮከብ እየተባለች በምትጠራው መቀሌና በሌሎችም የትግራይ አካባቢዎች በመተግበሩ ማህበሩ በጣም ደስተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ሀብቱ ካሳይ፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ስንሰራ የአካል ጉዳተኞችን ዘርፈ ብዙ ችግር መቅረፍ እንችላለን ሲሉ ቁልፍ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመቀጠል የካድር ፕሮጀክት የኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ግዛቸው ስለ ካድር ፕሮጀክት አጠቃላይ ይዘት ለታዳሚው ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ክልላዊ የፕሮጀክት አፈጻጸሙን በሚመለከት ደግሞ የማህበሩ የአካቶ ትምህርት ክፍል አስተባባሪና የኢኮኖሚ አቅም ግንባታ አስተባባሪ አጭር ገለጻ አድርገዋል።
በመጨረሻም አቶ ገብረ ስላሴ ታረቀኝና አቶ ሰለሞን ግዛቸው በአስተባባሪነት የመሩት ውይይት የተደረገ ሲሆን ከታዳሚው ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ አቶ ገብረ ስላሴ ታረቀኝ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ስነ ስርአቱ ተጠናቋል።


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Skip to content