በትናንትናው እለት ማለትም ሀምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ አይነስውራን ብሄራዊ ማኅበር በደብረብርሀን ይዞታው ላይ ያስገነባቸውን አራት ወፍጮዎች አስመረቀ፡፡


በደብረብርሀን እና አካባቢው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አዘጋጅነት እና አስተባባሪነት በተደረገው ፕሮግራም ላይ የኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር አመራሮች፣ የኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል የሆኑት ወ/ሪት ፍሬህይወት መዝገበ፣ ከደብረብርሀን ሪጆ ፖሊታንት ከተማ የመንግሥት መስሪያ ቤት ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ከቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ጋር በመተባበር ወፍጮዎችን ካስገነቡ አካላት እና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሠራተኞች እና አባላት ታድመዋል፡፡ በመርሀ ግብሩም ላይ የደብረብርሀን እና አካባቢው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኮሚቴ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ እና አቶ በዳሶ እንዳለ የኢትዮጵያ አይነስውራን ብሄራዊ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር የእንኳን ደህና መጣችሁ የሚል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ የማኅበሩ ፕሬዚደንትም የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በደብረ ብርሀን እና አካባቢው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ወደ ሌሎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችም መጋባት እንዳለበት፣ ልማትን ለማልማት መንገዱ ረጅም፣ ሂደቱ አድካሚ እና ውጣ ውረዱ አሰልቺ ቢሆንም ማፍረሱ እጅግ ቀላል በመሆኑ ልማቱን በአግባቡ ማስተዳደር እና ወደ ጥቅም መቀየር አሁንም በሚገባ መሠራት እንዳለበት እና ይህ ጅምር ሥራ የደብረ ብርሀን እና አካባቢውን ቅርንጫፍ ጽ/ቤትን ከዚህ በተሻለ መልኩ በማልማት ተመራጭ ማረፊያ ለማድረግ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ያመላከተ ነው በማለት የእለቱን መርሀ ግብር ከፍተዋል፡፡ በመቀጠል በመርሀ ግብሩ መሠረት የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እና ቀጣይ እቅዶች ቀርበዋል፡፡ በሙከራ ወቅት በነበረውም ሥራ ከተተከሉት አራት ወፍጮዎች ገቢ ማግኘት መጀመሩን፣ ለአምስት አዳዲስ ሰዎች የሥራ እድል መፈጠሩንና ሌሎችም መልካም ተግባራት መፈጸማቸውን በሪፖርቱ ተዳሰዋል፡፡ ከእቅድ እና ከሙዚቃዎች በኋላ፣ የማኅበሩ ፕሬዚደንት፣ የደብረብርሀን ከተማ ሴቶች ወጣቶች እና ህጻናት መምሪያ ኃላፊ በሆኑት ወ/ሮ በለጥሻቸው ግርማ እና በቅርንጫፍ ጽቤቱ የኮሚቴ ሰብሳቢ በሆኑት በአቶ ኤፍሬም መኩሪያ የተመራ የፓናል ውይይት ተደርጓል፡፡ በፓናል ውይይቱም ወቅት ከታዳሚዎች የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ወፍጮዎቹ የሚገኙበት የኢየሩሳሌም ቀበሌ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ደምስ፡- ወፍጮዎቹ ለረጅም ጊዜ የቀበሌዋ ነዋሪዎች ሲመኙት የነበረውን የልማት ጥያቄ የፈቱ መሆኑን በመጥቀስ ማኅበሩ ከአባላት አልፎ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ላደረገው ድጋፍ ከልብ አመሰግናለሁኝ ያሉ ሲሆን የማኅበሩን እግር ተከትሎ ሌሎች ባለሀብቶችም ወፍጮዎችን በቀበሌዋ ለመክፈት እየተንቀሳቀሱ ስለሆነ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት በደንብ መሠራት አለበት ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ከዚህ አስተያየት በተጨማሪም፣ ከቅጥር ጋር ተያይዞ፣ ከእቅድ እና ከሪፖርት አቀራረብ ጋር የተፈጠሩ ክፍተቶች እንዲብራሩ እና ከመንግሥት መስሪያ ቤቶች መስተንግዶ ጋር ተያይዞ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ለተነሱትም ጥያቄዎች የደብረብርሀን እና አካባቢው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ያብስራ፣ የኢትዮጵያ አይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር፣ አንዳንድ የደብረብርሀን እና አካባቢው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የኮሚቴ አባላት፣ አቶ ለማ፡- የደብረብርሀን ከተማ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ህጻናት መምሪያ የባለጉዳዮች ቡድን መሪ፣ ወ/ሮ በለጥሻቸው ግርማ እና የማኅበሩ ፕሬዚደንት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በዚህም መሠረት አቶ ያብስራ የወፍጮዎቹን እንቅስቃሴ እና ወደፊት የሚኖራቸውን ተስፋ በአግባቡ አብራርተዋል፡፡ ከከተማው የመንግሥት አካላት በተለይም ከወጣቶች፣ ከሴቶች እና ህጻናት መምሪያ ጋር ያለው የሥራ ቅንጅት በጣም የሚመሰገን መሆኑን፣ ሰራተኞች በቢሮ አይገኙም የሚለው አስተያየት ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው ወፍጮዎቹን በይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ እና ሌሎች ማብራሪያዎችንም ሰጥተዋል፡፡ የማኅበሩ ፕሬዚደንት በበኩላቸው፣ ከወፍጮዎቹ ውጭ በዚህ በደብረብርሀን ከተማ በሚገኝ ይዞታ ላይ ምን ሊሠራ ታቅዷል ለሚል እና ለሌሎችም ጥያቄዎች ሲመልሱ፡- ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት እስከ 1.5ቢሊየን የሚገመት ዋጋ ያላቸውን የልማት ሥራዎችን ለመሥራት በከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት እየሰራ መሆኑን፣ ማኅበሩ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ከተሞች ይዞታዎች ያሉት ቢሆንም ይዞታዎችን ለማልማት የፋይናንስ አለመኖር ለዘመናት ፈተና እንደሆነበት እና ይህንንም ችግር ለመቅረፍ እና ፋይናንስ በማፈላለጉ ረገድ መንግሥት ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ለማንኛውም ሥራ ፋይናንስ አብይ እና ቁልፍ ሀብት ነው ያሉት ፕሬዚደንቱ ማኅበሩ በይዞታዎቹ ላይ የልማት ሥራዎችን ለመሥራት የተሳነው በፋይናንስ እጥረት እንጂ በሌላ በምንም ምክንያት አይደለም ሲሉ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ሥራ አጥ አይነስውራንን ለመቀነስ እና ሥራ ላጡ አይነስውራን ሥራ እንዲያገኙ ለማድረግም ከውትወታ ጀምሮ ብዙ ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን በእቅድ ይዟል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የደብረ ብርሀን ከተማ ተሞክሮ በጣም ጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው ሌሎች ከተሞች፣ ክልሎች እና በፌደራል ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት አካላትም ተመሳሳይ አርአያ መከተል አለባቸው በማለት የደብረብርሀን ከተማ ለአካል ጉዳተኞች የሥራ እድል ለመፍጠር እና ሥራ አጥ አካል ጉዳተኞች እንዲያገኙ ወይም እንዲቀጠሩ እያደረገ ያለውን አበረታች አሰራር አወድሰው የእለቱን የፓናል ውይይት አጠቃለዋል፡፡ ከዚህ መርሀ ግብር በኋላ ልዩ ልዩ የምስጋና የምስክር ወረቀት ከደብረብርሀን እና አካባቢው ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለተለያዩ አጋር አካላት፣ ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቱን ለማጠናከር የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ እና ለጋሽ ድርጅቶች ተሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ያዘጋጀው ጣፋጭ የምሳ ግብዣ ከመልካም መስተንግዶ ጋር ለሁሉም ታዳሚዎች ተደርጎ የእለቱ መርሀ ግብር ተጠናቋል፡፡


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Skip to content