የወርክሾፕ ውሎ ማስታወሻ


መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓም የፍትሕ ሚኒስቴር እና ሴንተር ፎር ጀስቲስ በጋራ በመሆን ሚኒስቴሩ ባዘጋጀው ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ ላይ ግብዓት ለመሰብሰብ በዘሃብ ሆቴል በተሰናዳ የአንድ ቀን ፕሮግራም ላይ ተሳትፈናል።
አቶ ጉደታ ከፍትሕ ሚኒስቴር አዋጁን ለታዳሚዎች ሰፋ ባለ መልኩ አቅርበዋል።
ለአዋጁ መረቀቅ ገፊ ከሆኑት ምክንያቶች መካከልም በሕገ-መንግስቱና ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው አለማቀፍ ስምምነቶች ውስጥ የሚገኙ የሰብዓዊ መብቶች የበለጠ እንዲከበሩ ለማድረግ፣ የማህበራዊ ፍትህ ለማረጋገጥ፣ መክፈል ባለመቻል የፍትህ መጓደልን ለመከላከል፣ ለነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ለማበጀት፣ በሀገር አቀፍ ለሚሰጠው ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ያሉበትን ችግሮች በመቅረፍ ጥራት ያለው ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚሉ ይገኙበታል።
ሕጉ በትርጓሜ ክፍሉ ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ማለት በኢኮኖሚ አቅም ማነስ፣ በመብት ጥሰት ተጋላጭነት፣ ወይም የኢኮኖሚ አቅም ቢኖራቸውም ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት አገልግሎቱን በክፍያ ማግኘት ለማይችሉ ሰዎች ያለክፍያ የሚሰጥ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ነው በሚል ትርጉም ሰጥቶበታል።
‘የኢኮኖሚ አቅም የሌለው ሰው’ የሚለው ደግሞ ‘ባለው የገቢ ሁኔታ ወይም የኑሮ ደረጃ ምክንያት ከፍሎ የሚፈልገውን የህግ ድጋፍ አገልግሎት የማግኘት አቅም የሌለው ሰው ነው’ ተብሎ ተተርጉሟል። እንዲሁም በህጉ ‘የመብት ተጋላጭ የሆነ ሰው’ የሚለውን በእድሜ፣ በጤና ሁኔታ፣ ጾታ፣ አካል ጉዳተኝነት፣ የትምህርት ደረጃ፣ የአኗኗር ሁኔታ፣ ወይም በማንኛውም ማህበራዊ ወይም ሌላ ሁኔታ ምክንያት ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ካላገኘ በስተቀር የፍትህ መጓደል ሊደርስበት የሚችል ሰው ሲሆን ህጻናትን፣ ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን፣ ስደተኞችን፣ ለህገ ወጥ ፍልሰት የተጋለጡ ሰዎችን፣ የፍልሰት ተመላሾችን፣ ጾታን መሰረት ያደርገ ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች፣ አረጋውያንን፣ ያልተማሩ ወይም የትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛ በመሆን ለመብት ጥሰት የተጋለጡ ወይም ሊጋለጡ የሚችሉ ሰዎችን ያካትታል በማለት ሰፋ ያለ ትርጉም ሰጥቶበታል።
በረቂቅ ህጉ አንቀጽ 4 ስር የአዋጁ የተፈጻሚነት ወሰን በሀገር አቀፍ ደረጃ መሆኑን ተገንዝበናል።
ፈቃድን በተመለከተ በአዋጁ አንቀጽ 13 እና 14 ስር በህግ ነጻ የህግ ድጋፍ እንዲሰጡ ከተፈቀደላቸው ውጪ አገልግሎቱን ለመስጠት በፌደራል ደረጃ ከፍትህ ሚኒስቴር በክልል ደግሞ ከፍትህ ቢሮዎች ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባ፣ ፍቃዱም በያመቱ የሚታደስ እንደሆነ፣ በየ6 ወሩም የአፈጻጸም ሪፖርት የሚያስፈልግ እንደሆነ የሚያስቀምጥ መሆኑን ማወቅ ችለናል።
ፍቃድ ለማግኘትም ከተቀመጡት መስፈርቶች መካከል ለሲቪል ማህበርሰብ ድርጅቶች የተቀመጠውን ስንመለከት አንቀጽ 14 (2) (ሀ) ለምዝገባ በሚያቀርበው የመተዳደሪያ ደንብ የተቋቋመበትን አላማ፣ የሚሰጠው አገልግሎት አይነት፣ አገልግሎቱ ታሳቢ ያደረጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን፣ የተቋሙን የፋይናንስ አቅምና ምንጭ፣ የሰው ሀይል፣ የአገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች ብዛት፣ የትምህርት ዝግጅትና ስነምግባር፣ አገልግሎቱን የሚሰጥበት አካባቢ በግልጽ ማስቀመጥና አገልግሎት አሰጣጡ የሚመራባቸው ሁኔታዎችን በተገቢው ሁኔታ የሚገልጹ ሰነዶችን የማቅረብ እና ሌሎች በፍቃድ ሰጪው ሊጠየቁ የሚችሉ አስፈላጊ ሁኔታዎችን የሟሟላት፣ (ለ) አግባብነት ባላቸው ህጎች መሰርት ቢያንስ ፍቃድ ወስዶ በሚሰራበት አካባቢ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የጥብቅና ፈቃድ ለማግኘት የተጠቀሱትን የሥራ ልምድ፣ የስነ ምግባር መስፈርቶች የሚያሟላ ቢያንስ አንድ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ባለሙያ ያለው መሆን እና (ሕ) ቢሮን ጨምሮ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችሉ አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላት አለበት በሚል ተቀምጧል።
አዋጁ የነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ሰጪዎች እና ተጠቃሚዎች መብትና ግዴታ፣ የዲሲፕሊን ተጠያቂነትና ቅጣቶችን የያዙ ድንጋጌዎችን አቅፏል።
ረቂቅ አዋጁን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚመራ ምክር ቤት/ካውንስል ያቋቋመ ሲሆን፣ ስልጣንና ተግባሩንም ዘርዝሯል። በምክር ቤቱ አባልነትም የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮምሽን፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የክልል ፍትህ ቢሮዎች፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የክልል ጠቅላይ ፍ/ቤቶች፣ የፌደራል ጠበቆች ማህበር፣ የኢትዮጵያ የህግ ትምህርት ቤቶች ማህበር፣ ሴት የህግ ባለሙያዎች ማህበር እና የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን የተዘረዘሩ ሲሆን ውክልናንም በሚመለከት በተቋማቱ ኃላፊዎች እንደሆነ እና ሌሎች ተቋማት በምክር ቤቱ አባልነትም ሊጠቆሙ እንደሚችሉ በህጉ አንቀጽ 27 ስር ተመላክቷል።
በተጨማሪም ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ፈንድ በአዋጁ የተቋቋመ ሲሆን አላማውም የነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎትን ለመደገፍና ለማስፋት እንደሚውል በረቂቅ ህጉ ተቀምጧል። የፈንዱ የገንዘብ ምንጭም ከመንግስት፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከግለሰቦች ሊሆን እንደሚችል ተመላክቷል።
በአዋጁ ላይም ከዩኒቨርስቲዎች ጨምሮ ከሌሎች የመንግስት ተቋማት፣ ከሲቪል ማህበራት ድርጅቶች የተወከሉ ባለሙያዎች የበዙ ቢሻሻሉ እና ቢጨመሩ ያሏቸውን አስተያየቶች ሰጥተዋል። በረቂቁ ላይ ከተነሱ አስተያየቶችም መካከል አገልግሎቱ በነጻ የሚሰጥ እንደመሆኑ መጠን ፍቃድ ለማግኘት የቀርቡት መስፈርቶች ጠንካራ መሆናቸው ተገቢነት የሌለው መሆኑን እኛን ጨምሮ ብዙ ተሳታፊዎች አንስተዋል። ከዚሁም ጋር ተያይዞ በየአመቱ የፍቃድ እድሳት መጠየቁ ለዚህም ክፍያ ያስፈልጋል መባሉ በአገልግሎት ሰጪዎች ላይ ጫናን ስለሚፈጥር ቢያንስ እድሳቱ በየሶስት አመቱ ቢደረግ፣ አገልግሎቱ ነጻ እንደመሆኑ መጠን የእድሳት ክፍያውም ቢታይ የሚል ኃሳብ ቀርቧል።
ሌላው የተነሳው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ዝርዝር እና ፍቺው ላይ በጣም የሰፋና የተለጠጠ ስለሆነ ጠበብ ብሎ ቢቀመጥ የሚል ኃሳብም ተነስቷል። የምክር ቤቱ አባላት በስም መዘርዘራቸው በተለይ ተቋማቱ ስማቸው ሊቀየር ስለሚችል በጥቅል ከሴቶች፣ ከመንግስት፣ ከአካል ጉዳትኞች ማህበራት ተብሎ ቢቀርብ የሚል ኃሳብ ተነስቷል። ሌላው በአዋጁ በደንብ እና በመመሪያ ይወሰናል እየተባሉ የተቀመጡ ጉዳዮች አዋጁ በፍጥነት እንዳይፈጸም ተግዳሮት ሊሆኑ ስለሚችሉ አዋጁ ቀለል ብሎ ቢዘጋጅ በሚል ተነስቷል። የአካል ጉዳተኞች የነጻ ህግ ድጋፍ የማግኘት ጉዳይ በሚገባ በአዋጁ ቢመላከት እና በክልሎች የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ትኩረት ቢያገኙ እና ከዚህም አንጻር ቀለል ባለ መስፈርት አገልግሎቱን ማቅረብ የሚችሉ ተቋማትና ማህበራትን ማበረታታት ቢቻል በሚልም ሰፋ ያለ ኃሳብ ቀርቧል። ከዚሁም ጋር ተያይዞ ባለሙያ ማዘጋጀት እንደመስፈርት መቀመጡ እና የሚቀጠረው ባለሙያም የህግ ድግሪ እና ልምድ ያለው መሆኑን የሚጠይቀው መስፈርት ቀለል ብሎ ማህበራ ትወይም ተቋማት ባሏቸው ባለሙያዎች እንዲሰሩ ቢደረግ አዋጁ በአሁ ንሰዓት ያለውን የሰራተኛ ፍልሰት ከግምት ውስጥ በማስገባት ዲግሪ የሚለው መስፈርት ቢቀንስና ዲፕሎማ ያላቸውንም ሰራተኞች የሚቀጠሩበት ሁኔታ ቢመቻች የሚል ኃሳብ ቀርቧል።
የፍትህ ሚኒስቴር ተወካዮችም ከተሳታፊዎች የተሰጡት ግብዓቶች ጠቃሚ መሆናቸውን በመግለጽ አመስግነው ተቀብለው ህጉን ላረቀቁት ቡድኖች እንደሚያቀብሉ በመግለጽ የተወሰኑ ኃሳቦች ላይ ብቻ ማብራሪያ ሰጥተው ፕሮግራሙ መቋጫውን አግኝቷል።


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Skip to content