252ኛ የCCRDA ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ዘገባ


ማህበሩ የCCRDA አባል እንደመሆኑ በስብሰባው ላይ መሳተፍ ተችሏል፡፡ ስብሰባው ሲጀምር የድርጅቱ ዳሬክተር፣ የቦርድ ሰብሳቢና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዳሬክተር በየተራ ንግግር አድርገዋል፡፡ በተለይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዳሬክተር አስቸኳይ የፓርላማ ጥሪ ስለገጠማቸው ሊገኙ ያልቻሉትን የዋና ዳሬክተሩን የአቶ ሳምሶን ቢራቱን መልክት ካነበቡ በኋላ የራሳቸውን መልክት አስፍረዋል፡፡ በመልክታቸውም መንግስት ከሲቪል ማህበረሰቡ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ለመስራት በማቀዱ ባለስልጣኑ ራሱ በአባልነት የሚገኝበት አንድ የሲቪል ማህበረሰብ የጋራ ምክር ቤት እንደሚቋቋም ገልፀዋል፡፡ አስከትለውም ሲቪል ማህበረሰቡ፡- 1. ኃላፊነት በተመለከተ ስለድርጊቱ መናገር ብቻ ሳይሆን የሚያስከትለውን ውጤት በመገምገም ጭምር ሊሆን እንደሚገባና የሚወጡ መግለጫዎችን ከዚሁ አኳያ እንዲቃኙ፤ 2. ሲቪል ሶሳይቲው “በስማችን ተነገደ” የሚለውን አመለካከት በማስለወጥ ተቀባይነት እንዲያገኝ መስራት እንዳለበት፤ እና 3. ዘላቂ መሆን እንዲችሉና ሃብትን ከሀገር ውስጥ ለማፍራት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ሌላው ክንውን በተጓደሉ ሁለት የቦርድ አባላት ምትክ 1 ወንድና 1ሴት የቦርድ አባላት ምርጫ የተካሄደ ሲሆን ጥቆማ ከሰጡ አካላት መካከል የ4 እጩዎች ስም ለጉባኤው ቀርቧል፡፡ ከ4 መካከል የቱጌዘር ዳሬክተር አቶ ብርሀኑ በላይ የሚገኙበት ቢሆንም እሳቸውም ሆኑ ጠቋሚያቸው በቦታው ተገኝተው ለጉባኤው ማንነታቸውን አላስረዱም፡፡ ሌሎቹ 3ቱ ተጠቋሚዎች በግንባር ቀርበው ስለማንነታቸው አስረድተዋል፡፡ በተካሄደውም ምርጫ ወ/ሮ ሩት ወ/ተንሳይ የሚባሉ ሴት 115 ድምፅ ሲያመጡ አቶ መለሰ የተባሉ ሰው 98 ድምፅ አግኝተው የቦርዱ አባላት ሆነዋል፡፡ አቶ ዝናይ የተባሉ ሰው 18 ድምፅ አቶ ብርሀኑ በላይ 2 ድምፅ ሲያገኙ 4 ድምፅ መስጫ በትክክል ባለመሞላቱ ውድቅ ሆኗል፡፡
ሌላው የቀረበው ፁሁፍና ውይይት የተደረገበት የአሜሪካ የልማት ተራዶ ድርጅት ጉዳይ ሲሆን ኢትዮጲያን ጨምሮ በአለም ዙሪያ በርካታ ፕሮግራሞች ታጥፈው አንዳንድ ድርጅቶችም ሊዘጉ እንደሚችሉ በተለይ ግን ለኤች.አይ.ቪ መድሐኒት ተጠቃሚዎች መድሐኒቱ በመቋረጡ አደጋ ላይ መውደቃቸው ተብራርቷል፡፡ ይህን ለመቋቋም አማራጭ እርምጃ መውሰድ ስለሚያስፈልግ መንግስት ከአደጋ መከላከል ጋር አያይዞ ከወሰደው እርምጃ በተጨማሪ ሌሎችም አማራጮች ሊፈለጉ እንደሚገባ ተጠቅሶ ለጥናት የተላከ ሊንክ ድርጅቶቹ እንዲሞሉ ተጠይቋል፡፡
ሌላው የድርጅቱ የ2024 የክንውን ሪፖርትና የውጪ ኦዲተር የተመረመረ የኦዲት ሪፖርት እንዲሁም 2025 ዓ.ም ዕቅድ ቀርቦ ፀድቋል፡፡ ራስን ለመቻ በሚደረገው ጥረት ጂ+5 የሆነ ሕንፃ ለመገንባት ታቅዶ ዲዛይኑ በመጠናቀቁ ለተሰብሳቢዎቹ ቀርቦ ገለፃ ተደርጓል፡፡ ከዚህ የገዘፈ ህንፃ ለመስራት የሚያስችል መሬት በከተማ አስተዳደሩ ተፈቅዶ የነበረ ቢሆንም ወጪው ከድርጅቱ አቅም በላይ በመሆኑ ሳይቀበሉት መቅረታቸውን ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቢዝነስ አካል መቋቋም እንደሚያስፈልግ ታምኖበት ድርጅቱ ቋሚ የቢዝነስ አካል እንዲያቋቁም ተወስኗል፡፡
በስተመጨረሻ አዲስ አባላትን ለመቀበል አጀንዳ ቀርቦ 44 ድርጅቶች ለአባልነት ቢያመለክቱም በቦርድ ተገምግሞ ተቀባይነት ያገኙ የ36 ድርጅቶች አባልነት ፀድቋል፡፡


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Skip to content