በሙያና ቴክኒክ አካታችነት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሄደ።


የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር የሙያና ቴክኒክ ተቋማትን አካታችነት ለማረጋገጥ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተከታታይነት ያላቸው ስራዎችን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል። በ2017 የሰኔ ወር አጋማሽ ላይ ከስዊዲን አይነስውራን ማህበር በአፍሪካ ህብረት በኩል በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ የዚህ ስራ አንዱ አካል የሆነ የምክክር ወርክሾፕ በአዳማ ከተማ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር መደረጉ ይታወሳል።
የሙያና ቴክኒክ ተቋማትን አካታች የማድረግ ጥረቱ አሁንም የቀጠለ ሲሆን ከኖርዌ መንግስት በኖርዌ አይነ ስውራንና ከፊል እይታ ያላቸው ማህበር በኩል የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎለት እየተተገበረ ባለው የካድር ፕሮጀክት አማካኝነት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተጨማሪ የምክክር ወርክሾፕ ተካሂዷል። ውይይቱ የተካሄደው ቅዳሜ ነሀሴ 3 ቀን 2017 አ.ም ከሰአት በኋላ በማህበራችን ጽ/ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሲሆን በውይይት መድረኩ የማህበራችን ፕሬዝዳንት አቶ አበራ ረታ፣ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ፋንታሁን መንግስቴ፣ ከማህበሩ ጽ/ቤት ማኔጅመንት አባላትና ሰራተኞች፣ ከአባላት፣ ከአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከመምህራንና ሴቶች ዘርፍ እንዲሁም አይነ ስውራንን በመቅጠር ከሚታወቁ አምራች ድርጅቶች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ለውይይቱ መነሻ እንዲሆን “The Challenges and Prospects of Peoples with Disabilities to Join Technic Institutions” ወይም ወደ አማረኛ ሲመለስ “አካል ጉዳተኞች በሙያና ቴክኒክ ተቋማት ገብተው ለመማር የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶችና ያሉ የተስፋ ጭላንጭሎች” በሚል ርእስ በፌደራል ሙያና ቴክኒክ ኢኒስቲቲውት የተካሄደ ጥናት ቀርቧል። ጥናቱን ያቀረቡት ጥናቱን በመሪ ተመራማሪነት ያካሄዱት ወ/ሮ ጥሩዬ አበበና አቶ ሰውአገኝ ሞላ ሲሆኑ በፌደራል ሙያና ቴክኒክ ተቋም የሚያስተምሩ ምሁራን ናቸው።
በቀረበው ጥናት ላይ እንደተገለጸው ለአካል ጉዳተኞች ካላቸው ምቹነት አንጻር የተለያዩ መስፈርቶችን በመጠቀም የሙያና ቴክኒክ ተቋማቱን ለመገምገም ተሞክሯል። ጥናቱ ከአመለካከት አኳያ የሙያና ቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ለአካል ጉዳተኞች የሚሆኑ አይደሉም ብለው የሚያምኑ ጥቂት አመራሮችና ሰራተኞች መኖራቸውን አመላክቷል። ከመምህራን ብቃት አንጻር በአካቶ የስልጠናና ትምህርት አሰጣጥ ስነዘዴ ላይ እውቀት ያላቸው መምህራን ቁጥር አነስተኛ መሆኑንም እንዲሁ ጥናቱ አሳይቷል። አብዛኞቹ የማሰልጠኛ ማሽኖች ሁሉም ሰልጣኝ በእኩልነት ሊጠቀምባቸው የሚችሉ የአለማቀፍ ዲዛይን መመዘኛዎችን የማያሟሉ መሆኑ በጥናቱ ከታዩ ክፍተቶች መሀል ይገኝበታል። በጥናቱ ከተካተቱ ተቋማት መካከል አብዛኞቹ ለአካል ጉዳተኞች እንቅስቃሴ ምቹ የሆነ አካባቢያዊ ገጽታ የሌላቸው መሆኑና ለአካል ጉዳተኞች በተለይም ደግሞ ለአይነ ስውራን አመቺ የሆኑ የስልጠና ዘርፎች አለመኖራቸውንም ጥናቱ አሳይቷል ተብሏል።
በአካል ጉዳተኞች በተለይም በአይነ ስውራን በኩል የቀለም ትምህርትን እንደ ብቸኛ የህይወት አማራጭ አድርጎ መውሰድና በሙያና ስልጠና ተቋማት ገብቶ ለመማር ፍላጎት አለመኖር፤ በሙያና ቴክኒክ ተቋማት ለሚሰጡ ስልጠናዎች ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ መሆንና ከሚወክሏቸው ማህበራት ጋር ተቀራርበው በጉዳዩ ላይ አለመስራት በአካል ጉዳተኛ ሰልጣኞች በኩል የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል።
ከባለድርሻ አካላት አንጻር የአካል ጉዳተኛ ማህበራትና መንግስት በሙያና ቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና አካታችነት ዙሪያ ተቀናጅተው እየሰሩ አለመሆኑ፤ የሙያና ቴክኒክ ስልጠናን በተመለከተ በአባሎቻቸው ዘንድ የሚስተዋለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቅረፍ የሚሰሩት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ አነስተኛ መሆኑና ከሙያና ቴክኒክ ተቋማት ጋርም ተቀራርቦ መስራት ላይ ሰፊ ክፍተት ያለባቸው መሆኑን ያጠኑት ጥናት እንደሚያሳይ አቶ ሰውአገኝና ወ/ሮ ጥሩዬ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከፖሊሲዎችና የህግ ማእቀፎች አኳያ የተወሰኑ ክፍተቶች ቢኖሩም ያን ያህል የጎሉ አለመሆናቸውና እነሱም ቢሆኑ በሂደት ሊስተካከሉ የሚችሉ መሆናቸው ተገልጿል። ትልቁ ችግር አተገባበር ላይ እንደሆነ ጥናታቸው ያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።
ከጥናቱ በኋላ ውይይት የተደረገ ሲሆን በተለይም ደግሞ ለአይነ ስውራን አመቺ የሆኑ የስልጠና ዘርፎች አለመኖራቸውን በማስመልከት ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በዚህም መሰረት የመጥረጊያና መወልወያ፣ የጸጉር ስራ፣ ማሳጅ፣ ዣንጥላ ጥገና፣ ምንጣፍ ስራ፣ የሹራብ ስራ፣ ሙዚቃ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የሳሙና ምርት፣ የንግድ ስራ፣ የስልክ ኦፕሬተርነት፣ የጌጣጌጥ ስራዎች፣ ሻማ ማምረት፣ ምግብ ዝግጅት ፣ መስተንግዶ፣ ግብርና፣ የጨርቃጨርቅ ስራዎች፣ ጽዳትና የመሳሰሉት ስራዎች የትምህርት ስርአት ቢቀረጽላቸው በሙያና ቴክኒክ ተቋማት አይነ ስውራን ሰልጣኞች ሊሰለጥኑባቸው የሚችሉ ዘርፎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በአሁኑ የሙያና ስልጠና ስርአተ ትምህርት የተካተቱ የስልጠና ዘርፎችን በዝርዝር ማየታቸውን የገለጹ አንድ ተሳታፊ በስርአተ ትምህርቱ ከታቀፉ 192 ዘርፎች መካከል አብዛኞቹ አይነ ስውራን ወይም ከፊል እይታ ያላቸው ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል፤ በአጭር ጊዜ ወይም በረጅም ጊዜ ሊሰለጥኑባቸው የሚችሉ ናቸው የሚል እምነት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ተወክለው በመድረኩ ላይ የተገኙት ባለሙያ በበኩላቸው አይነ ስውራን ሊሰለጥኑባቸው ይችላሉ ተብለው በተሳታፊዎች የተዘረዘሩት አብዛኞቹ በስርአተ ትምህርቱ ላይ የታቀፉ መሆኑን፤ ያልታቀፉ እንኳን ቢኖሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስርአተ ትምህርት ተቀርጾላቸው እንዲሰራባቸው ማድረግ እንደሚቻል አጽእኖት ሰጥተው ተናግረዋል። በሙያና ቴክኒክ ተቋማት በኩል ጥናቱ ያሳያቸው ክፍተቶች እውነት መሆናቸውን የተናገሩት ባለሙያው፣ በትግበራ ሂደት ሁሉም ነገር ይስተካከላል ብለዋል። ይሁንና በተቋማት ላይ ያለው ሁኔታ ምቹ አይደለም በሚል ምክኒያት ዝም ብሎ ከመቀመጥ ይልቅ አሁን ባለው እድል ተጠቅመው አይነ ስውራን ወደ ሙያና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ቢመጡ በትግበራ ሂደት በርካታ ነገሮችን ማሻሻል እንደሚቻል በልበ ሙሉነት ተናግረዋል።
በመጨረሻም ማህበሩና ስራና ክህሎት ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሙያና ቴክኒክ ተቋማት አሰራር ላይ ያለው ክፍተት እንዲታረም በጋራ እንዲሰሩበትና አሁን ያሉ የስልጠና ዘርፎችን የማስተዋወቅና ሌሎች በስልጠና ማእቀፍ መታቀፍ አለባቸው በሚባሉ ስልጠናዎች ዙሪያ ለአይነ ስውራን ግንዛቤ እንዲሰጥና በቀጣይ የሚመጣውን ለውጥ እያዩ የመስራት አስፈላጊነት ላይ በመግባባት የውይይት መድረኩ ተጠናቋል።
እኛም ይህን እንላለን። ከዚህ ዘገባ ጋር ተያይዞ የቀረበውን የአጫጭር ጊዜ ስልጠና ዝርዝር በመመልከት የትኞቹ አይነ ስውራን ሊሰማሩባቸው የሚችሉ ናቸው ብላችሁ ታምናላችሁ። ካልተካተቱስ የትኞቹ ዘርፎች ቢካተቱ ትላላችሁ። አስተያየቶቻችሁን ጻፉልን።


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Skip to content