በሀረር ከተማ ፕሮጀክት የማስጀመሪያና የውይይት ፕሮግራም ተደረገ


የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር የሚመራውና የሚያስተባብረው በቅርቡ የተጀመረው የካድር ፕሮጀክት (Collective Action on Disability Rights) በሚተገበርባቸው አከባቢዎች ፕሮጀክቱን የማስጀመርና የማስተዋወቅ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። የነዚህ ፕሮግራሞች ዓላማም የባለድርሻ አካላት ስለፕሮጀክቱ አውቀው ለትግበራው የበኩላቸውን አበርክቶ እንዲያደርጉና፣ የባለድርሻ አካላቱ ፕሮጀክቱን በየኔነት ስሜት አይተው የዓይነስውራንን ብሎም የሌሎች አካል ጉዳተኞችን መብቶች እንዲያከብሩ፣ እእንዲጠብቁና እንዲያስተዋውቁ በአጠቃላይም ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ አካቶና ተጠቃሚነት እንዲሠሩ ለማድረግ ነው።
የዚሁ ፕሮጀክቱን የማስጀመርና የውይይት ስነስርዓት አካል የሆነውን ፕሮግራም ፕሮጀክቱ ከሚተገበርባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው በሀረር ከተማ ነሀሴ 7 ቀን 2017 ዓም ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ ከተለያዩ ከመንግስት ተቋማት የተወከሉ ተሳታፊዎች፣ የማኅበራችን አባላትና ሌሎች የባለድርሻ አካላት ፕሮግራሙን ታድመዋል። የማኅበራችን ፕሬዚደንት አቶ አበራ ረታ በመድረኩ በመገኘት ፕሮግራሙን በከፈቱበት ንግግራቸው የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ለሌሎች የአካል ጉዳተኛ ማኅበራት ምስረታ አስተዋጽኦ ያደረገ ጠንካራና አንጋፋ ማኅበር ስለመሆኑ ያወሱ ሲሆን፣ አንጋፋነቱንና ጥንካሬውን የሚመጥኑ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ለተሳታፊዎች አስረድተዋል። ፕሮጀክቱን አስመልክተውም፣ በትብብርና በላቀ የባለቤትነት ስሜት መሥራት ከተቻለ በሀረር ከተማና አካባቢዋ የሚገኙ ዓይነስውራንንና ሌሎች አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻል መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም፣ ለፕሮጀክቱ ትግበራ መሳካት የባለድርሻ አካላት የሚጫወቱት ሚና ትልቅ እንደሆነና በአብሮነትና በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ መፍቱሃ አሊዪ ስለፕሮጀክቱ በከተማዋ መተግበር የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ፣ ይህ እንዲሳካ ላደረገው ለኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ለፕሮጀክቱ መሳካትም ተቋማቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ ላይ ስለፕሮጀክቱ ሰፋ ያለ ገለጻ ተደርጎ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል። እንዲሁም፣ መብትን በማስከበር፣ በከተማዋና አካባቢው የሚሠራውን የማኅበራችንን ቅርንጫፍ ጽ/ቤትን ከማጠናከርና በአጠቃላይ በጋራ በመሥራት ረገድ ማኅበራት በሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ተችሏል።


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Skip to content