ምዝገባውን ያከናወኑት የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበርና የፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ብሄራዊ ማህበር በጋራ በመሆን ነው። ሁለቱ እህትማማች ማህበራት የካድር ፕሮጀክትን በጋራ እየተገበሩ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከ2 ሳምንታት በፊት በሀዋሳ ከተማ አካል ጉዳተኛ ልጆች ላሏቸው ወላጆችና ተንከባካቢዎች ስልጠና መስጠታቸው ይታወሳል። የዚህ ፕሮጀክት ቀጣይ የስራ አካል የሆነው ከትምህርት ቤት ውጪ ያሉ አካል ጉዳተኞችን የመመዝገብ ስራ ከነሀሴ 5 እስከ ነሀሴ 11 2017 አ.ም ድረስ ባሉት 6 ተከታታይ ቀናት በሀዋሳ ከተማ ታቦርና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ተከናውኗል።
የቤት ለቤት ምዝገባው ከመከናወኑ አስቀድሞ ከሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮና ከከተማው ትምህርት ጽ/ቤት የልዩ ፍላጎት ትምህርት ተጠሪዎች ጋር ውይይት ተደርጓል። በውይይቱ ስለሁለቱም ማህበራትና በጋራ በመተግበር ላይ ስላሉት የካድር ፕሮጀክት ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል። በመቀጠልም በታቦርና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሊካሄድ ስለታሰበው ከትምህርት ውጪ የሆኑ አካል ጉዳተኞችን የመመዝገብ ዘመቻ ማብራሪያ ከተሰጣቸው በኋላ ከበጎ ፈቃደኛ መዝጋቢዎች ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱ መደምደሚያ የሀዋሳ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ለመዝጋቢዎቹ ማንነታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንዲሰጣቸው፣ በመዝጋቢዎቹ በኩል በሚጠበቅባቸው የስነ ምግባር ልክ እንዲሰሩና የጸጥታ ችግር ሊፈጥርባቸው የሚችል አካል ካለ በቀጥታ ሪፖርት እንዲያደርጉ፣ ስራቸውን ከመንደርና ከብሎክ አስተባባሪዎች ጋር በመሆን እንዲያከናውኑና የተጠቃለለውን የምዝገባ ሪፖርት ለጽ/ቤቱም እንዲያስረክቡ መግባባት ላይ ተደርሷል።
ለበጎ ፈቃደኞቹ ምዝገባው ከመካሄዱ አስቀድሞ በምዝገባው ላይ ስለሚጠቀሙባቸው የተለያዩ ቅጾች ማብራሪያና የተግባር ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። የተለያዩ አካል ጉዳቶች ያሉባቸውን ሰዎች ለመለየት በሚጠቀሙበት የዋሽንግተን አካል ጉዳተኞችን የመለያ ቅጽ ላይ ትኩረት ያደረገ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል። በመጨረሻም የመመዝገቢያ ቅጻቅጾች ርክክብ ከተደረገ በኋላ በቀጥታ ምዝገባ ወደማካሄድ እንዲገቡ ተደርጓል።
ለተከታታይ ቀናት ሲደረግ የነበረው ትምህርት ያቋረጡ ወይም እድሜያቸው ለትምህርት ደርሶ ወደ ትምህርት ቤት ያልተላኩ አካል ጉዳተኛ ልጆችን የመመዝገብ ስራው ተጠናቆ ሪፖርቱ የተጠናቀረ ሲሆን በሪፖርቱ መሰረት በዘመቻው 74 ሴትና 55 ወንድ በድምሩ 129 አካል ጉዳተኞችን መመዝገብ ተችሏል። ከእነዚህ አካል ጉዳተኞች ውስጥ ሰባ ዘጠኙ ከ18 አመት በታች ሀምሳው ደግሞ ከ18 አመት በላይ ናቸው።
የአካል ጉዳት ስብጥራቸውን ስንመለከት አስራ ሁለቱ አይነ ስውራን፣ 1 መስማት የተሳነው፣ 29 የእንቅስቃሴ አካል ጉዳት ያለባቸው፣ 65 የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው፣ 1 የተግባቦት ችግር ያለበት እንዲሁም ሀያአንድ ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው ናቸው። በቀጣይ ለእነዚህ አካል ጉዳተኞች ጠለቅ ያለ የህክምና ምርመራ በማድረግ የአካል ጉዳታቸው መጠን ከተለየ በኋላ ህክምና የሚያስፈልጋቸው የህክምና ክትትል እንዲደረግላቸውና ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ የማድረግና የህክምና ክትትል የማያስፈልጋቸውን በተመሳሳይ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ በማድረግ በትምህርት ቤት ውስጥ አስፈላጊው የትምህርት ቁሳቁስና የስነ ልቦና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዲማሩ የማድረግ ስራ የሚከናወን ይሆናል።

Leave a Reply