በአካል ጉዳተኞች መብት አጠባበቅ ዙሪያ የሚዲያ ባለሙያዎች ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ!


የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሔራዊ ማኅበር (ኢዓብማ) ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የሚዲያ ባለሙያዎች የአካል ጉዳተኞችን መብትና ተሳትፎ በተመለከተ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም በተሳካ ሁኔታ አከናውኗል። የዚህ ፕሮግራም ዋነኛ ዓላማ ሚዲያዎች የአካል ጉዳተኞችን መብት በማስፋፋት እና በተለይም አይነ ስውራንን በተመለከተ ያለውን የሕብረተሰብ አመለካከት በመለወጥ ረገድ ያላቸውን ሚና ማጠናከር ሲሆን፣ ዝርዝር አላማዎቹም የሚዲያ ባለሙያዎች እንደ አጠቃላይ ስለ አካል ጉዳተኞች በተለይ ደግሞ ስለ አይነ ስውራን መብት ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ፤ አካል ጉዳተኞች ሚዛናዊ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ ማገዝ እና የአካል ጉዳተኝነት መብት ተሟጋችነትን በተመለከተ በኢዓብማ እና በሚዲያ አካላት መካከል ስትራቴጂካዊ ትብብር መፍጠር ናቸው። የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩን በገንዘብ የደገፈው በአፍሪካ አይነ ስውራን ህብረት በኩል የስዊዲን አይነ ስውራን ማህበር ሲሆን በመድረኩ ከ15 የተለያዩ ብሔራዊና አካባቢያዊ የቴሌቪዥን፣ የሬዲዮ፣ የህትመትና የዲጂታል ሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ ጋዜጠኞች፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሙያዎች፣ የተወሰኑ የማህበራችን የጠቅላላ ጉባኤ አባላትና የጽ/ቤታችን ሰራተኞችን ጨምሮ በአጠቃላይ 30 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። በኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር የአፍሪካ አይነ ስውራን ህብረት ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክትን እያስተባበሩ ያሉት አቶ ከተማ ባይለየኝ በኢዓብማ አደረጃጀት እና በፕሮጀክቱ ዳራ ላይ ያተኮረ የመክፈቻ ንግግር ካደረጉ በኋላ የሥልጠናው ዋና ክፍል በዶ/ር ዮሐንስ ታከለ አማካኝነት የተሰጠ ሲሆን በዚህም የአካል ጉዳተኝነት ትርጉም፣ የአካል ጉዳተኝነት ሞዴሎች፣ አካታች የሚዲያ ዘገባዎች፣ ትክክለኛ የቃላት አጠቃቀም እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችን መብት በማስፋፋት ረገድ ሚዲያው ያለው ሚና ላይ ጥልቅ ውይይቶች ተደርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ የሕግ ማዕቀፎች፣ ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረጉ የአካል ጉዳተኝነት ጽንሰ ሀሳቦች እና አካታች የጋዜጠኝነት ልምዶች የቀረቡ ሲሆን ጋዜጠኞች የአካል ጉዳተኞች ጉዳይን እንዴት በበለጠ ገንቢ በሆነ መንገድ ማቅረብ እንደሚችሉ ውይይት ተደርጓል። በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ቴክኒካል ጥያቄዎች ዶክተር ዮሀንስ ታከለ ሙያዊ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ማህበሩን አስመልክቶ ለተነሱ አስተያየቶች ደግሞ የማህበሩ ዋና ስራ አስኪሀጅ አቶ በዳሶ እንዳለ ምልከታቸውን አንጸባርቀዋል። ስራ አስኪሀጁ የሚዲያ ባለሙያዎች ወደ ስራቸው ሲመለሱ ለአካል ጉዳተኞች መብት መከበር ሚና የሚጫወቱ ፕሮግራሞችን ወደ ህዝብ እንዲያደርሱ፣ ወደ ኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር በመምጣት የተለያዩ መጽሀፍትን እያነበቡ በመቀረጽ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን እንዲሰሩ፤ የማህበሩን እንቅስቃሴዎች በመዘገብ ማህበረሰቡ ስለ አይነ ስውራን ያለው ግንዛቤን ከፍ እንዲያደርጉና አይነ ስውራን ወደ ሚዲያው ዘርፍ እንዲመጡ ለማድረግ ሙያዊ እገዛ በማድረግ እንዲተባበሩ አደራ ካሉ በኋላ በቀጣይም ማህበሩ ለአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ጠቃሚ የሆኑ ተመሳሳይ ስልጠናዎችን እንደሚያዘጋጅ ቃል ገብተዋል። በመጨረሻም አቶ በዳሶ ለዚህ ዝግጅት ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉት ለአፍሪካ አይነ ስውራን ህብረትና የስዊዲን አይነ ስውራን ማህበር፣ ግንዛቤውን ለሰጡት ዶክተር ዮሃንስ ታከለ፣ ለሁሉም ተሳታፊዎች እና ለጽ/ቤት ሰራተኞች ምስጋና በማቅረብ የመድረኩን መጠናቀቅ አብስረዋል። ማስታወሻ። በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ ተሳታፊ ከነበሩ ጋዜጠኞች መካከል ከ ሶስቱ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ በተከታታይ ክፍሎች እናቀርባለን። ለቃለ ምልልሱ አጠቃላይ ስራ የአዳማና አካባቢዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ባልቻ ጀንበሬን ከልብ እናመሰግናለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Skip to content