በኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር መሪ አስተባባሪነት ከናታኒም የበጎ አድራጎት ድርጅት እና ከፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውሱንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማኅበር ጋር በጋራ በመሆን የሚተገበረው የካድር ፕሮጀክት በድሬደዋ ከተማ ነሀሴ 6 ቀን 2017 ዓም በተሰናዳው ፕሮግራም ላይ የፕሮጀክቱ ፈጻሚ አካላት አመራሮች በተገኙበት ፕሮጀክቱን ለባለድርሻ አካላት የማስተዋወቅ እና የውይይት ፕሮግራም ተካሂዷል። በፕሮግራሙ ላይም ቁልፍ የመንግስት ተቋማት አመራሮች፣ ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት የተወከሉ ተሳታፊዎች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የአካል ጉዳተኛ ማኅበራት አመራሮች እና የሚዲያ ተቋማት ታድመዋል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የማሕበራችን ፕሬዚደንት አቶ አበራ ረታ ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ለዓይነስውራን ብሎም ለሌሎች አካል ጉዳተኞች መብቶች መከበር እያደረገ ያለውን አበርክቶ ለተሳታፊዎች በመግለጽ ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን፣ አክለውም፣ ፕሮጀክቱ የዓይነስውራን ብሎም የሌሎች አካል ጉዳተኞች መብቶች በተሟላ ደረጃ እንዲከበሩ በማድረግ ረገድ ይዞ ለተነሳው ዓላማ ግብ መምታት የባለድርሻ አካላት ያላቸው ሚና ከፍ ያለ መሆኑን በመግለጽ፣ ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በጋራ እና በርብርብ እንሥራ በሚል ለፕሮግራሙ ታዳሚዎች ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ኤጀንሲ ኃላፊ የሆኑት አቶ አብዱራህማን ሙሳ የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ስለፕሮጀክቱ መምጣትና ማኅበሩ ስለሚሠራቸው ሥራዎች በማመስገን ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን፣ በመቀጠልም፣ የፕሮጀክቱ መምጣት በድሬደዋ እና አካባቢዋ ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በንግግራቸው አንስተው፣ የፕሮጀክቱ መምጣትን እንደትልቅ ምስራች እንደሚያዩ ገልጸዋል።
ስለፕሮጀክቱ አጠቃላይ ሁኔታ ለተሳታፊዎች አጭር ገለጻ የተደረገ ሲሆን፣ ከመድረክ ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ከፕሮጀክት ባለሙያዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል። በተጨማሪም፣ በአካል ጉዳተኞች መብቶች አከባበር ዙሪያ አጠር ያለ ገለጻ በባለሙያ የተደረገ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች በቡድን ተከፋፍለው የአካል ጉዳተኞች መብቶችን በማክበር፣ ማስከበር እና በማስተዋወቅ ዙሪያ ሊጫወቱ የሚገባቸውን ሚና በተመለከተ ተወያይተው ቀጣይ አቅጣጫ (Way Forward) እንዲያስቀምጡ ማድረግ ተችሏል።

Leave a Reply