ማህበራችን ከአራዳ ክፍለ ከተማ ትራፊክ ጽ/ቤት እና ከወረዳ 6 ሰላምና ጸጥታ ጋር በመነጋገር ጽ/ቤታችን በሚገኝበት ማለትም ከየካቲት 12 ሰማእታት መታሰቢያ ሆስፒታል ወደ ናዝሬት እስኩል በሚወስደው ቴድሮስ በሚል ስያሜ በሚታወቀው መንገድ ላይ በርካታ አይነ ስውራን የሚንቀሳቀሱ መሆኑን በማስረዳት፤ በመንገዱ ላይ መኪና ማቆም እንዲከለከልና በ1 አቅጣጫ ብቻ ማሽከርከር እንዲፈቀድ ይህንንም የሚያመላክቱ የትራፊክ ምልክቶች እንዲተከሉ ማድረጉ ይታወሳል። ይሁንና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ምልክቶቹ በመነሳታቸው አይነ ስውራን በመንገዱ ላይ በሚቆሙና ከሁለቱም አቅጣጫ በሚመጡ ተሽከርካሪዎች ሲቸገሩ መቆየታቸው ይታወቃል። ማህበራችንም ምልክቶቹ በድጋሚ እንዲተከሉ በተደጋጋሚ ሲወተውት የቆየ ሲሆን ዘግይቶም ቢሆን ውትወታው ፍሬ አፍርቶ በድጋሚ ምልክቶቹ እንዲተከሉ ማድረግ ተችሏል። የክፍለ ከተማው ትራፊክ ጽ/ቤትና የወረዳ 6 ሰላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ምልክቶቹን የማስከበር ሀላፊነት ያለባቸው በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ የሚሰሩ ሲሆን ከዚህ ባለፈ የህግ አስከባሪ አካላት በአካባቢው አለመኖርን በማየት የትራፊክ ህግ ጥሰት የሚፈጽሙ አሽከርካሪዎችን የተሽከርካሪ ታርጋ ቁጥር በመያዝ ለወረዳ 6 ሰላምና ጸጥታ ጽ/ቤት መጠቆም የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን።

Leave a Reply