
ኢትዮጵያ አይነ-ስውራን ብሄራዊ ማህበር ከሀምሌ 19 እስከ ሀምሌ 20 2017 አ.ም በአክሱም ከተማ በያሬድ ዜማ ሆቴል የካድር ፕሮጀክት የመክፈቻ ስነ-ስርአት እና አካታች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ስልጠና ከልዩ ልዩ የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ አካል ጉዳተኛ ማህበራት እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው 29 የሚሆኑ (8ሴት እና 21ወንድ) ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።
የመክፈቻ ስነ ስርአቱን በእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስጀመሩት አቶ የማነ ዮሀንስ በኢትዮጵያ አይነ-ስውራን ብሄራዊ ማህበር የአክሱም እና አካባቢዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሰብሳቢ ሲሆኑ፣ በመቀጠል አቶ ገብሬ ተሾመ የማህበሩ ማኔጅመንት አባል ማህበሩን በመወከል ለፕሮግራሙ ታዳሚ ቁልፍ መልእክት አስተላልፈዋል። ማህበሩ ለበርካታ ጊዜያት በትግራይ ክልል አክሱም ከተማን ጨምሮ የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ለማፈላለግ ሲሞክር የቆየ መሆኑን የገለጹት አቶ ገብሬ ተሾመ፣ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለጋሽ አካላት በክልሉ ለሚደረጉ የፕሮጀክት ሀሳቦች ዝግ እንደነበሩ አስታውሰዋል። ይሁንና ማህበሩ ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት ዛሬ እየተከፈተ ያለውን ፕሮጀክት ወደ ክልሉ ለማምጣት መቻሉን አስረድተዋል። ፕሮጀክቱ በክልሉ በመተግበሩ ማህበሩ በጣም ደስተኛ መሆኑን ገልጸው አብሮ መስራትን በማጠናከር ተያይዘን ስንሰራ የአካል ጉዳተኞችን ዘርፈ ብዙ ችግር መቅረፍ እንችላለን ሲሉ ቁልፍ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመቀጠል የካድር ፕሮጀክት የኢኮኖሚ ልማት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ አያሌው ስለ ካድር ፕሮጀክት አጠቃላይ ይዘት እና በአክሱም ከተማ የሚተገበሩ ስራዎች ላይ ለታዳሚው ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በመቀጠልም አጠቃላይ ውይይት በተሳታፊዎች ተካሂዷል።
በመጨረሻም በአካል ጉዳተኞች አካታችነት፣ በተደራሽ የኢኮኖሚ ልማት ህግና ፖሊሲ ትግበራ ዙሪያ ያተኮረ ሁለት ቀናትን የወሰደ ስልጠና በህግ ባለሙያ የተሰጠ ሲሆን በአጠቃላይ አካል ጉዳተኞችን የሚመለከቱ ህጎች፣ አካታች ፖሊሲዎችና አተገባበራቸው ላይ በመንግስት ሴክተር መ//ቤቶች ያለውን የአካቶ ትግበራ ሁኔታን በመገምገም ከሴክተር መ/ቤቶች ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ውጤታማ ውይይት ተደርጓል።
በስልጠናው ተሳታፊዎች ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ያላቸውን መልካም ተሞክሮና ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች አካፍለዋል። በቀጣይ መሻሻል ያለባቸውን ስራዎች በመለየትም በሴክተር ደረጃ መውሰድ የሚገባቸውን ሀላፊነት በመስጠት በስኬት ተጠናቋል።


Leave a Reply