የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበርና ፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ብሄራዊ ማህበር በመቀናጀት አካል ጉዳተኛ ልጆች ላሏቸው ወላጆች በሀዋሳ ከተማ ሴንትራል ሆቴል ስልጠና የሰጡ ሲሆን ስልጠናው ያተኮረው የአእምሮ እድገት ውስንነት ምንነት፣ የአካል ጉዳተኛ ህጻናት መብት፣ አይነ ስውራን ህጻናት በመኖሪያ ቤትና በአካባቢያቸው ሊፈጠርላቸው ስለሚገቡ ምቹ ሁኔታዎች፣ ወላጆች ከራሳቸው ልጆች አልፎ በአካባቢያቸው የሚገኙ ህጻናትን ወደ ት/ቤት እንዲገቡ መውሰድ ስለሚገባቸው እርምጃዎችና ከመንግስታዊ አካላት ጋር እንዴት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችንም ያካተተ ነበር።
ስልጠናውን የሰጡት በፍቅር ኢትዮጵያ በኩል ወ/ሮ ፋንታዬ ተክሌ ሲሆኑ በኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር በኩል ደግሞ አቶ ወግደረስ እጅጉና አቶ ከተማ ባይለየኝ ናቸው። በስልጠናው ወቅትና ከስልጠናው በኋላ ወላጆች የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። በዚህም እስከዛሬ ድረስ ልጆቻቸውን ሳይንሳዊ ባልሆነ መንገድ ሲረዱ የቆዩ መሆናቸውንና ከዚህ በኋላ ግን ከስልጠናው ባገኙት እውቀት መሰረት መኖሪያ ቤታቸውን ጨምሮ አካባቢያቸውን በሙሉ ለአካል ጉዳተኛ ልጆቻቸው ምቹ በማድረግ ለስኬታቸው እንደወላጅ የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ህጻናት ከታፈኑበት እንዲወጡና የትምህርት እድል እንዲያገኙ ለማድረግ በእየመዋቅሩ ከሚገኙ የመንግስት ተቋማት ጋር ለመስራት ያላቸውን ተነሳሽነት አሳይተዋል።
በመጨረሻም የፍቅር ኢትዮጵያ የትምህርት ክፍል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ፍጹም ወርቅነህ የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበርና ፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ማህበር ከወላጆች ጋር በመሆን የአካል ጉዳተኛ ህጻናት መብት እንዲከበር ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ በመግለጽ የእለቱ ስልጠና ተጠናቋል።

Leave a Reply