አጭር የስብሰባ ውሎ ማስታወሻ – በመኮንን


ትላንት ህዳር 30 ቀን 2017 ዓም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህበረት (ኢሰመድህ) በThe Hub Hotel ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶችን አፈጻጸም አስመልክቶ በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በኩል በሚዘጋጀው በአራተኛው ዙር ሁለንተናዊ የአቻ ግምገማ ወቅት የተሰጧትን ምክረ-ሀሳቦች በተመለከተ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር ውይይት ለማድረግ በተሰናዳው ፕሮግራም ላይ ተሳትፈናል።
በዚህ ውይይት ላይ የተለያዩ የሲቪል ማህበራት የተገኙ ሲሆን ሀገራችን በቅርቡ በጄኔቫ ተገኝታ የሰብዓዊ መብቶችን አፈጻጸም አቅርባ ምክይረ-ሀሳብ መቀበሏን በተመለከተ ቀደም ሲል ወሬውን እዚህ መግለጻችን ይታወሳል። ማኅበራችንም አማራጭ ሪፖርት በመሪነት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ማስገባትንም እንደዚሁ።
ትላንት በነበረው ውይይት አቶ ዩሱፍ ከፍትሕ ሚኒስቴር ውይይቱን የመሩ ሲሆን፣ ሀግራችን በአራተኛው ዙር በተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ ያተኮሩ 316 ምክረ-ሀሳቦችን መቀበሏን ገልጸዋል። ከነዚህም መካከል 15ቱ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የተሰጡ መሆናቸውንም እንደዚሁ።
ምክረ-ሀሳቦቹ ለተሳታፊዎች የቀረቡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም ድርጂቶቻቸው እንደሚያተኩሩበት መብት በቡድን በቡድን በመሆን በመከፋፈል ምክረ-ሀሳቦቹን አይተናል። አቶ ዩሱፍ በሰጡት መመሪያ መሰረት እያንዳንዱን ምክረ-ሀሳብ የምንቀበለውን ወይም ሀገራችን ብትቀበለው ጥሩ ነው ያልነውን accept እንድንልና ባትቀበል የምንለውን noted እያልን እንድናስቀምጥ፣ noted ማለት ደግሞ አለመቀበል ስለሆነ ምክንያታችንን እንድናስቀምጥ በማለት መመሪያ ሰጥተው ውይይት ተደርጓል። እኛም rights of specific persons በሚለው ሥር ስለአካል ጉዳተኞች የተሰጡትን ምክረ-ሀሳቦች አይተን ሁሉን ብትቀበል በሚል አቅርበናል። በተለይም በሰነዱ አንቀጽ 58.297 እና 58.298 ሥር በተለይም ደቡብ ሱዳንና ሀንጋሪ ስለአካል ጉዳተኞች ህግ ማውጣትን የተመለከቱት ላይ በተሰጠን እድል ተጠቅመን ትኩረት ቢሰጠው በሚል አቅርበናል።
በዚህ ውይይት ላይ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አዝመራው፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፋሲካውን ጨምሮ ሌሎች የድርጅት መሪዎች እንዲሁም ከጤና፣ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ፣ እንዲሁም ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የተወከሉ አካላት የተገኙበት ጥሩ ውይይት ተደርጓል። አቶ ፋሲካውና አቶ አዝመራው ዘለግ ያለ ንግግር ያደረጉ ሲሆን አብዛኛው የንግግራቸው ትኩረት የነበረው ስለሲቪል ማህበረሰቦች ሚና፣ ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ ስላላቸው አበርክቶ እንዲሁም ስለፕሮግራሙ አዘጋጆችና ስለተሳታፊዎች ስላላቸው ምስጋና ነበር።
አጠቃላይ በአራተኛው ዙር ለሀገራችን ከአቻ ሀገራት የተሰጣት ምክረ-ሀሳብ ከዚህ ወሬ ጋር ተያይዟል። ይህ ሰነድ በተለያዩ መብቶች ላይ ጥናት ለማድረግ፣ የአድቮኬሲ ሥራዎች ለመስራት፣ ፕሮጀክት ለመቅረጽ ወዘተ ጠቃሚ ስለሆኑ በአንክሮ ቢታዩ እንላለን።


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Skip to content