በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ከፊል እይታ ላላቸው የማህበሩ አባላት ስልጠና ተሰጠ።


ስልጠናው ከካድር ፕሮጀክት (Collective Action on Disability Right) የጤና ዘርፍ ተግባራት አንዱ አካል ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አይነ-ስውራን ብሄራዊ ማህበር ከናታኔም በጎ አድራጎት ማህበር እና ከአለርት ሆስፒታል ጋር በመተባበር የተሰጠ ነው። ለሁለት ቀናት የተካሄደው ስልጠና ዋና ዓላማ ከፊል እይታ ያላቸው አባላት እይታቸው እንዲቀንስ የሚያደርጉ መነሻ ምክኒያቶችን ተረድተው የአይናቸውን ጤና እንዲጠብቁ እንዲሁም አእምሯዊ፣ ስነልቦናዊና ማህበራዊ ጤናማነትን ለመንከባከብ መወሰድ ስላለባቸው የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች እንዲገነዘቡ ማድረግ ነው። ከዚህ ባሻገር ምን አይነት የህክምና እርዳታ ማግኘት እንደሚችሉ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የተደረገ ሲሆን ከናታኔም በጎ አድራጎት ድርጅት የመጡ የስነ-ልቦና ባለሙያዎች ከአይነ-ስውርነት ጋር ተያይዞ የሚመጡ ማህበራዊ ችግሮች እና ተግዳሮቶች ላይ እንዲሁም ተግዳሮቶችን እንዴት ማለፍ እንደሚቻል ግንዛቤ አስጨብጠዋል።
ስልጠናው ስኬታማ እንደነበር ከሰልጣኞች ከተሰጡ አስተያየቶች መረዳት የተቻለ ሲሆን ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን፣ ችግሮቻቸውን እንዲሁም ስጋቶቻቸውን በነጻነት ገልጸዋል። በመድረኩ ከተነሱ አስተያየቶች መካከል ገዝፎ የተነሳው ማህበሩ እና ፕሮጀክቱ ህክምና ለማግኘት አቅም ለሌላቸው አባላት ለህክምና ወጪ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግበት መንገድ ቢኖር የሚል አስተያየት ነበር።
በሌላ በኩል ከሰልጣኞች መካከል ፍቃደኛ ለሆኑ አባላት የእይታ ልኬት ምርመራ የተደረገ ሲሆን 6 የሚሆኑ አባላት ተጨማሪ ምርመራና ህክምና የሚያስፈልጋቸው መሆኑ ተለይቷል። እነዚህ አባላት ተጨማሪ ምርመራና ህክምና እንዲያገኙ በሪፈራል አገልግሎት ወደተመረጡ ሆስፒታሎች እንደሚላኩ ተገልጿል። ይህ ስልጠና በአዲስ አበባ የመጀመሪያው ዙር ሲሆን በተመረጡ ሌሎች ከተማዎች እና በሌላ ዙር በአዲስ አበባ የሚቀጥል ይሆናል።


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Skip to content