የፈለገኪን የኪነጥበብ ፕሮግራምን የአንድ አመት ጉዞ በተመለከተ የፕሮግራሙ አስተባባሪ ኮሚቴ ነሀሴ ሶስት እለተ ቅዳሜ 2017 አ.ም ከቀኑ ሶስት ሰአት ተኩል እስከሰባት ሰአት በኢትዮጲያ አይነስውራን ብሄራዊ ማህበር ግቢ የመሰብሰቢያ ኣዳራሽ የአንድ አመቱን የፕሮግራሙን ጉዞ የሚመለከት የውይይት መድረክ ኣዘጋጅቶ ነበር።


በእለቱም የኢትዮጲያ አይነስውራን ብሄራዊ ማህበር የቦርድ ፕሬዝዳንት አቶ ኣበራ ረታ፣ የኢትዮጲያ አይነስውራን ብሄራዊ ማህበር ስራ አስኪያጅ በዳሶ እንዳለ፣ በማህበሩ የአባላት ጉዳዮችና የህዝብግኑኝነት ሃላፊ የሆኑትን አቶ ገብሬ ተሾመን ጨምሮ ጉዳዩ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሚመለከታቸው በኢትዮጲያ አይነስውራን ብሄራዊ ማህበር ያሉ የተለያዩ የስራ ክፍል ሃላፊዎች ሲገኙ፤ በፈለገኪን የኪነጥበብ መድረክ ስራዎቻቸውን በቋሚነት የሚያቀርቡ የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች፣ የተመረጡ የፕሮግራሙ ቋሚ ታዳሚዎችና ነባር የወጋገን ባንድ ኣባላትም ተገኝተው ነበር።
በመድረኩም የፈለገኪን የኪነጥበብ መድረክን የአንድ ኣመት ጉዞ ጥቅል ሁኔታ የሚያስገነዝብ ሪፖርት በፕሮግራሙ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኢሳያስ ባንጫ ቀርቦ ነበር። ሪፖርቱ በኣራት ምእራፎች በመከፋፈልም የፈለገኪን የኪነጥበብ ፕሮግራምን ጽንሰትና ኣጀማመር፣ የፈለገኪን የኪነጥበብ ፕሮግራምን የአንድ አመት ጉዞ፣ ፈለገኪን ለማህበሩ የፈጠራቸውን እድሎችና በፕሮግራሙ የአዘገጃጀትና አመደራረክ ወቅት የነበሩ ፈተናዎችን የሚዳስስ ነበር። ከሪፖርቱም በኋላ የፈለገኪን የኪነጥበብ መድረክ አስተባባሪዎችን የወደፊት እቅድ የሚያስገነዝብ ጽሁፍ በኮሚቴው ጸሃፊ አቶ ጌታቸው ሞገስ ቀርቧል። እቅዱም የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ ተብሎ ለሁለት የተከፈለ ሲሆን በጥቅሉ ፕሮግራሙን ከፍ ባለ ሁኔታ ለመመድረክና ጠንካራ፣ ዘላቂና ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሃሳቦችን ያካተተ ነበር። በስራ ክንውን ሪፖርቱና የፕሮግራሙ የወደፊት እቅድ ላይ ተመስርተውም የፕሮግራሙ ታዳሚዎች አስተያየትና ጥያቄ አንስተዋል።
ሲጠቃለል ከተሳታፊዎቹ የቀረቡት አስተያየቶችና ጥያቄዎች የፕሮግራሙን ቅርጽና ይዘት፣ የፕሮግራሙ ቋሚ ተሳታፊዎች ሊያገኟቸው የሚገቡትን ጥቅማጥቅም፣ የፕሮግራሙን ጥራት ሁኔታና በፕሮግራሙ የእስካሁን ጉዞ ያለመታከት የተጉ የፕሮግራሙ አስተባባሪ ኮሚቴዎችንና የፕሮግራሙን ባለቤት ብሄራዊ ማህበሩን ማመስገንን የሚመለከቱ ነበሩ። በጉዳዩ ላይም የፈለገኪን የኪነጥበብ ፕሮግራም አስተባባሪ ኮሚቴዎች፣ የኢትዮጲያ አይነስውራን ብሄራዊ ማህበር የቦርድ ፕሬዝዳንት አቶ አበራ ረታ፣ የማህበሩ ስራአስኪያጅ አቶ በዳሶ እንዳለና የወጋገን ባንድ አስተባባሪ የሆነው ቢኒያም ሳእለ ማብራሪያ ሰተዋል።
በማብራሪያቸውም የፈለገኪን የኪነጥበብ ፕሮግራም አስተባባሪ ኮሚቴዎች የፕሮግራሙን ቅርጽና ይዘት ኪናዊ ለዛ ያለው እንዲሆን ጥበባዊነትን በተላበሰ መልኩ ተገቢውን ማሻሻያ ማድረግ ያለውን ኣስፈላጊነት በመገንዘብ ለዚህም አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ቃል ገብተዋል። የማህበሩ ባለድርሻ አካላትም የፈለገኪን የኪነጥበብ ፕሮግራም እንደተቋም ለኢትዮጲያ አይነስውራን ብሄራዊ ማህበር የገጽታ ግንባታ፤ እንደአንድ የማህበረሰብ ክፍል ደሞ አይነስውራን ከኪነጥበብ ጋር ሊኖራቸው የሚገባን ትውውቅን አስመልክቶ፤ ተሰጧቸውን ከማዳበር አኳያም ሆነ እርስ በእርስና ከሌሎች ማህበረሰቦችጋር ለሚኖራቸው ግኑኝነት በጎ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ፤ የማህበሩ አሰራርና አቅም በፈቀደ መጠን ፕሮግራሙን በተለየ ቁርጠኝነት ለማስቀጠል ያላቸውን ድጋፍና ለዚህም በጋራ መስራት ያለውን ኣስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። በጥቅሉ የውይይት መድረኩ የኪነጥበብ ፕሮግራሙን ጥራት ለማሳደግ በነጻነት ሃሳብ የተንሸራሸረበት ከመሆኑ ባሻገር በፈለገኪን የወጋገን ባንድ ኣባላት የሙዚቃ ስራና በፈለገኪን ስነጽሁፍ አቅራቢዎች ግጥም የደመቀም ነበር።
በዚህ አጋጣሚ ፈለገኪን እለተ ቅዳሜ ነሃሴ 24 ሜክሲኮ በሚገኘው የወመዘክር አዳራሽ የፕሮግራሙን የእስካሁን ተጋባዥ እንግዶችና ሌሎች የባለድርሻ አካላትንም ጋብዞ አንደኛ አመቱን በልዩ ድምቀት ለማክበር መሰናዶውን በማጧጧፍ ላይ ይገኛል። በእለቱም አይነስውራን ወገኖቻችን ብትችሉ አይናማ ወዳጆቻችሁን ጋብዛችሁ በመገኘት የፕሮግራሙ ድምቀት አካል ትሆኑ ዘንድ የፕሮግራሙ አስተባባሪ ኮሚቴ በክብር ጥሪውን ያቀርባል።

የተስፋችን ብስራት፣ በመክሊታችን ኩራት።
የፈለገኪን አስተባባሪ ኮሚቴ፣
ነሀሴ 5 ቀን 2017 አመተ ምህረት።
አዲስ አበባ።


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Skip to content