ዛሬ የካቲት 20 ቀን 2018 ዓም በአዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ዓይነስውራን ምቹና ተደራሽ የባንክ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ ላይ የስልጠናና የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።
መድረኩ የተዘጋጀው ባንኮች ለዓይነስውራን ምቹና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት ያለባቸውን ግዴታ ለማስገንዘብ፣ እንዲሁም ባንኮች ምቹና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት የሚገጥሟቸውን ችግሮች በመረዳት የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ለመወያየት ነው።
በዚህ መደረክ ላይ ከተለያዩ የንግድ ባንኮች የተወከሉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ከብሔራዊ ባንክ እና ከኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር የተወከሉ ኃላፊዎች የፕሮግራሙ ታዳሚ ሆነዋል።
በዝግጅቱ ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዚደንት አቶ አበራ ረታ ማኅበሩ ቀደም ሲል ለረጅም ዓመታት በባንክ ተደራሽነት ዙሪያ የሠራቸውን የአድቮኬሲና የውትወታ ሥራዎች በማስታወስ ዛሬ የተዘጋጀውን ፕሮግራም ዓላማዎች በዝርዝር አቅርበዋል። በንግግራቸውም፣ በርካታ ዓይነስውራን ከተለያዩ የባንክ አገልግሎቶች ተገልለው እንደሚገኙ እና ከፋይናንስ አካታችነት አንጻር ንግድ ባንኮች እና ብሔራዊ ባንክ እንደየድርሻቸው ብዙ እንደሚጠበቅባቸው አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። እኛ ዓይነስውራን ተደራሽ የባንክ አገልግሎት እንደ ሰማይ ርቆናል በማለትም ምሬታቸውን ገልጸዋል። ባንኮች የሚሰጧቸው ምርቶች (Products) እና አገልግሎቶች ለዓይነስውራን ተደራሽ እና ምቹ ለማድረግ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ለዚህም አበክረው እንዲሠሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በፕሮግራሙ ላይ በባለሙያ አማካኝነት ዓይነስውራን በባንክ አገልግሎት ማግኘት ዙሪያ የሚገጥሟቸውን የተለያዩ ተግዳሮቶች በዝርዝር ለተሳታፊዎች ማቅረብ የተቻለ ሲሆን፣ የፕሮግራሙ ታዳሚዎችም በዝርዝር ከባንክ አሠራር፣ ከቴክኖሎጂ እና ከሕግ አኳያ የሚገጥሙ ችግሮችንና የመፍትሔ ኃሳቦችን ጠቁመዋል። ከመድረኩ የባንክ አሰራር ወጥነት አለመኖር እና በበጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ በሚመስል ደረጃ በአንድ ቅርንጫፍ የሚሰጥ አገልግሎት በሌላው ስለመከልከሉ፣ ከዚህም አንጻር ባንኮች የሚከተሉት የአሰራር መመሪያ መኖር አለመኖሩ የተጠየቀ ሲሆን፣ የበዙ የንግድ ባንኮች ተወካዮች የግንዛቤ እጥረትን፣ ባንኮች አሠራሮቻቸውን በሚገባ ከተደራሽነት አኳያ ስልጠና አለመስጠታቸውን እና ሌሎች ጉዳዮችን እንደክፍተት በማንሳት ሆን ተብሎ ግን አገልግሎት እንደማይከለከል፣ ዓይነስውራን አገልግሎቶች ሲጠይቁ መታወቂያ እና ምስክር የሚጠየቀው ለራሳቸው ጥበቃ መሆኑን በመግለጽ አስተያየት የሰጡ ሲሆን አንዳንድ ተሳታፊዎች በውስጥ የኃላፊ የማረጋገጫ ፊርማን (Approval) ብቻ በመጠቀም አንድ ዓይነስውር መታወቂያ እና ምስክር የሚያመጣበትን የአሠራር ሂደት መተዋቸውን በመግለጽ ልምዳቸውን አካፍለዋል።
ተሳታፊዎች በመድረኩ የተነሱ ከተደራሽነት ጋር የተያያዙና መሰል ችግሮችን ለመፍታት በግል እንደሚጥሩ እና ለተጨማሪ ውይይትና አቅጣጫም ከመድረኩ የተገኙ ፍሬ ኃሳቦችን ወስደው ከበላይ ኃላፊዎች ጋር እንደሚወያዩም ቃል ገብተዋል።
ከመድረኩ እና ከፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ለብሔራዊ ባንክ ተወካዮች የመመሪያ መውጣት ጉዳይ በጥያቄ መልክ በስፋት የተነሳ ሲሆን፣ የባንኩ ተወካዮች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ብሔራዊ ባንክ በአሁኑ ሰዓት አዳዲስ መዋቅሮችን እየዘረጋ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፣ ቀደም ሲል የነበረው ‘Banking and Supervision Directorate’ በአዲሱ መዋቅር ‘Regulation, Licensing and Approval Department’ በሚል መዋቀሩን ጠቅሰው፣ የአካል ጉዳተኞች የባንክ ተደራሽነት መመሪያ በአዲሱ ክፍል በዚህ ዓመት ለመውጣት ከተዘጋጁ መመሪያዎች መካከል እንደሚገኝበት ተናግረዋል። አክለውም፣ በአሁኑ ሰዓት ረቂቅ (Zero Draft) መዘጋጀቱን እና በቅርብ ጊዜ ለባለድርሻ አካላት ለአስተያየት እንደሚላክም ጠቁመዋል።
በመጨረሻም፣ የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ለመድረኩ መዘጋጀት ማኅበሩን አመስግነው ፕሮግራሙ ባንኮች ተደራሽነት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ የሚያሳስብ እንደ አንቂ ደወልም የሚቆጠር መሆኑን በመግለጽ የባንኮች አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።
የባንክ ተደራሽነት ጉዳይ ከፍተኛ ችግር እንደመሆኑ መጠን፣ ማኅበሩ ከግንዛቤ ማስጨበጥና መሰል ፕሮግራሞች ጎን ለጎን ስልታዊ ሙግትን በመጠቀም ለዓይነስውራን ተደራሽ አገልግሎት የማይሰጡ ባንኮች እና መሰል የገንዘብ ተቋማት ላይ በፍ/ቤት ክስ ማቅረብ ይፈልጋል። ከዚህ አንጻር ችግሮች የሚገጥሟችሁ አባላት ጉዳዩን ማኅበሩ ለፍ/ቤት እንዲያቀርብ ፍቃደኝነታችሁን በመግለጽ የገጠሟችሁን ችግሮች እዚህ መጠቆም የምትችሉና ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት እንዲሄድም በአካል በጽ/ቤት በመቅረብ ማሳወቅ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን።



Leave a Reply